በመቀሌና በባህርዳር ከነማ የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል በተፈጠረው ግጭት የባህርዳር ከነማ ጥፋተኛ ሆኖ እንዲቀጣ ውሳኔ ተላለፈ

ኢሳት (ግንቦት 8 ፥ 2009)

በመቀሌ ከነማና በባህርዳር አቻው የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል በተፈጠረው ውዝግብና ግጭት የባህርዳር ከነማ ጥፋተኛ ሆኖ እንዲቀጣ ውሳኔ መተላለፉን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል የተላለፈው ውሳኔ የፊታችን አርብ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። 

ዕርምጃው ፖለቲካው ይዘት ያለው ነው የሚለውን ለመከላከል ከዳኞቹና ከውድድር ኮሚቴ በተገኘ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ውሳኔው መተላለፉን የሚገልጽ ደብዳቤ መዘጋጀም ትመአልክቷል።

የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ወደዚህ ውሳኔ የተገፋው ግን በፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

የመቀሌ ከነማ ቡድንን ጥፋተኛ ማድረግ ሌሎች ክልሎችም እንዲነሳሱ ስለሚያደርግ የባህርዳርን ቡድን ጥፋተኛ አድርጎ መቅጣት ተመራጭ ሆኖ መገኘቱንም ለመረዳት ተችሏል።

በጨዋታው የመቀሌ ደጋፊዎች በዘር ላይ የተመሰረተ ስድብ ሲያስተጋቡ በመዋላቸው ጨዋታው ወደሃይል ተቀይሮ ለግጭት መዳረጉና ለባህርዳር ተጫዋቾች መጎዳት ምክንያት መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።