በሃረር በከፍተኛ የውሃ ችግር ተከስቷል። ከ1 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ያላነሰ ገንዘብ የወጣባቸው ፕሮጀክቶች ተቋርጠዋል።

መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የ747 ሚሊዮን 175 ሺ ብር ብድር የተሰራው የሃሳሊሶ የውሃ ፐሮጀክት ለ30 አመታት ለ350 ሺ ህዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንደሚያቀርብ፣ በ2004 ዓም ሲመረቅ የመንግስት ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ ውሃው ሸሽቷል በሚል ምክንያት ተመርቆ 2 አመታት እንኳ በአግባቡ ሳያገለግል የተዘጋ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት ሃረር በከፍተኛ የውሃ እጥረት በመሰቃየት ላይ ናት። ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ የከተማው ህዝብ ከጉድጓድ የሚቀዳ ውሃ በውድ ዋጋ እየገዛ ለመጠቀም ተገዷል።
በፕሮጀክቱ ላይ ሲየም የተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ በአማካሪነት፣ የቻይና ኮንስትራክሽንና እና ኦቨርሲስ ኩባንያ፣ በሲቪል ግንባታ ስራዎች፣ የህንድ ኩባንያ የሆነው የኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ የፓምፕ እና ፓናል ቦርድ ግዢ እና ተከላ ፣ የኔዘርላንድ ቬቲንስ ኢቪዴስ አንተርናሽናል ድርጅት በ37 ሚሊዮን ብር በውሃው ያለውን የካልሲየም ባይካርቦኔት ስራ ለመስራት በፕሮጀክቱ ላይ ተሳትፈው ነበር።
የሃረሪ ክልል እና የኦሮምያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌ ዞን በባቢሌ ወረዳ ስር የሚገኘው ኤረር ሸለቆ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ በተገመተ ወጪ 7 ከፍተኛ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቢቆፈሩም፣ የባቢሌ መስተዳደር ባነሳው የክፍያ ጥያቄ በተፈጠረው ውዝግብ ጉዳዩ ከኦሮምያ ክልል ምላሽ እስከሚጥበት በሚል ስራው እንዲቆም ከተደረገ በሁዋላ፣ ክልሉ በ 5 ቀበሌዎች ውሃ እንደሚሰጠው ቃል በተገባለት መሰረት ስራው ቢጀመርም በመብራት እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እስካሁን ስራ አልጀመረም። በብሄር ብሄረሰቦች ቀን ፕሮጀክቱ እንዳለቀ ተደርጎ ቢነገርም፣ እስካሁን ስራ አልጀመረም።
የሃሰሊሶ ውሃ የተቆፈረው በሃረሪ ክልል ተበዳሪነትና ወጪ አድራጊነት ሲሆን የድሬዳዋ መስተዳደርና የኦሮምያ ምስራቅ ሃረርጌ ዞን መስተዳደር ውሃው ካላካፈላችሁኝ አናስቆፍርም ፣ በመንገዳችንም አናስኬድም በማለታቸው፣ በድርድር ከድሬዳዋ መስተዳደር የሃሰሊሶ ቀ/ገ/ማ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ አካዳሚ፣ የገነት መናፈሻ አካባቢ፣ የጀሉበሊናና ሃርሳ ገጠር ቀበሌዎች፣ ከምስራቅ ሃረርጌ ዞን አስተዳደር ደግሞ ደንገጎ፣ አደሌ፣ ሃሮማያ ከተማ፣ ሃሮማያ ዩኒቨርስቲ፣ አወዳይ ከተማ እና የወሌንቦ ገጠር ቀበሌ ተጠቃሚ እንዲሆን ስምምነት ተደርሶ ነበር።
በቅርቡ የብሄር ብሄረሰቦች በአል በሃረር ከተማ ሲከበር፣ ነዋሪዎች የውሃ ችግራችን ይቀረፍልናል ብለው ሲጠብቁ፣ የመንግስት ሰራተኞች ሙሉ ደሞዛቸውን፣ ነጋዴዎችም እንዲሁ ከፍተኛ መዋጮ እንዲከፍሉ ከተደረገ በሁዋላ፣ መንግስት በመደበው ተጨማሪ ገንዘብ ውሃ ቀርቶ ስታዲየም እንዲገነባ የተደረገ ሲሆን፣ ስታዲየሙም 25 በመቶ ብቻ እንደተገነባ ስራውን የሚሰራው ከህወሃት ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው አፍረጺዮን ኩባንያ፣ ስራውን በማቋረጥ ወደ አፋር በመሄድ ሌላ ተመሳሳይ ስታዲየም በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ወጪ እየሰራ ሲሆን፣ የሃረር ስታዲየም ምንም አገልግሎት ሳይሰጥ ባለበት መቆሙን የከተማ ነዋሪዎች በቁጭት ይናገራሉ።
ለዚሁ በአል ተብሎ በቻይና ኩባንያ በፍጥነት እንዲሰራና ለበአሉ እንዲደርስ ተብሎ የተሰራው የአስቫልት መንግ መስመር ሰሞኑን በጣለው ዝናብ ተጠርጎ በመኖሪያ ቤቶች ላይ በማረፉ ብዙ ጉዳት አድርሷል።
ከብሄር ብሄረሰቦች በአል ማግስት የውሃ ችግራችንን ሳይፈታ፣ ስታዲየም የተባለውም ሙሉ በሙሉ ሳይገነባ፣ አስፋልቱም በውሃ ተጠርጎ ጥሩ አገልግሎት ሳይሰጥ፣ ለችግር ተዳርገናል በማለት ነዋሪዎች ምሬታቸውን ይገልጻሉ።
በአሁኑ ሰአት አንድ ጀሪካን የጉድጓድ ውሃ በ10 እና በ15 ብር እየተሸጠ መሆኑን እንዲሁም የውሃ እጥረቱን ተከትሎ የውሃ ልማት ሃላፊዎች ለባለስልጣናት እና የተሻለ ገንዘብ ለሚከፍሉዋቸው ባለሀብቶች እየመረጡ ውሃ በመልቀቅ ላይ መሆናቸውነዋሪዎች አክለው ይናገራሉ።
ከአፍሪካ ባንክ በተገኘ ብድር የተሰራውና 750 ሚሊዮን ብር አካባቢ የወጣበት የጃራ ( ሃለሊሶ ) የውሃ ፕሮጀክት ለመዘጋቱ የተሰጠው ምክንያት ውሃው ከጉድጓዱ ሸሽቷል የሚል ነው።