በሃረር ለሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የመንግስት ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዝ እንዲያስረክቡ ተገደዱ

ጥቅምት ፲፰ (አሥራ ስምንት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ሰራተኞች ለኢሳት እንደገለጹት ለበአሉ የተመደበው 500 ሚሊዮን ብር በማለቁ ፣ የመንግስት ሰራተኛው የአንድ ወር ደሞዙን እንዲያስረክብ እየተገደደ ነው። መመሪያው ከላይ አመራሮች የወረደ ሲሆን፣ ታች ያሉት አመራሮች በስራቸው ላሉ ሰራተኞችን እንዲነግሩ ታዘዋል።

ሰራተኞች “ አገዛዙን ይወረድ እያልን እየጠየቅን ባለበት በዚህ ወቅት ፣ ደሞዛችሁን እንወሰዳለን መባሉ ድፍረት ነው” በማለት ተቃውሞአቸውን እያገለጹ ነው። ውሳኔው ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

ክልሉ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር እንዳጋጠመው ለማወቅ ተችሎአል። ፌደራል መንግስት ለበአሉ ማክበሪያ ብሎ ከመደበው ግማሽ ቢሊዮን ገንዘብ ውስጥ 300 ሚሊዮን ብር የቻይና ኩባንያ ለሚገነባው መንገድ ወጪ ሲሆን፣ 200 ሚሊዮኑ ደግሞ ለጽዳትና ውበት ወጪ ይሆናል። መንገድ የማስጌጥ ስራው በእያመቱ የሚዘጋጁ በአላትን የሚያዘጋጁት የህወሃት አባላት ሃላፊነት ወስደው ይሰሩታል።