መንግስት ከቆሼ መደርመስ ለተረፉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ምንም ድጋፍ አላደረገም ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 18 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ በቆሻሻ ክምር መደርመስ የተረፉት ከ325 በላይ ነዋሪዎች በመንግስት በኩል የተደረገላቸው ምንም አይነት ድጋፍ እንደሌለ ገለጹ።

በቆሻሻ ክምር ናዳው እናቱን፣ አባቱን፣ እህቶቹን፣ አያቱን ጨምሮ 7 ቤተሰቦቹን ያጣው ወጣት አስረስ እውነቱ ለኢሳት እንደገለጸው ከአደጋው የተረፉትና በአካባቢው ያሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢውን እንዲለቁ በመንግስት ታዘዋል። ይህም ሆኖ አካባቢውን ሲለቁ መንግስት መጠለያም ሆነ መቋቋሚያ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጸዋል።

አስረስ እውነቱ የተባለው ወጣት ጉዳተኛ ለኢሳት እንደተናግረው ተጎጂዎቹ አካባቢው በአስቸኳይ እንዲለቁ መንግስት ግዴታ የጣለባቸው የቆሼ አካባቢ ነዋሪዎች ቤት ተከራይተው ወይም ዘመድ ፈልገው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።

ቤተሰቦቹን በቆሻሻ መደርመስ ያጣው ይኸው ወጣት የአዲስ አበባ ህዝብ ለአደጋ ተጎጂዎች ላደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርቦ፣ ህዝቡ አሁንም ድረስ ምግብና አልባሳትን እያበረከተ እንደሆነ ገልጿል።

በመደርመስ አደጋ የሞቱ ሰዎችን ፍለጋ አሁንም ድረስ የቀጠለ መሆኑን የገለጹት የተጎጂ ቤተሰቦች፣ ብዙ ሰዎች በቆሻሻው ተቀብረው ሊገኙ እንደሚችሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል።