ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ደመወዛችን አይቆረጥብንም ያሉ የመንግስት ሰራተኞች ” ጸረ-ሰላም ሀይሎች ” የሚል ደብዳቤ እየደረሳቸው ነው

ህዳር 28 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-

በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ደመወዛችን አይቆረጥብንም ያሉ የመንግስት ሰራተኞች ” ጸረ-ሰላም ሀይሎች ” የሚል ደብዳቤ እየደረሳቸው ነው።

የተለያዩ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ለኢሳት የደቡብ ዘጋቢ እንደገለጡት፣ የኢትዮጵያ የሰራተኛ አሰሪ አዋጅ አንድ ሰው ደመወዙን ያለራሱ ፈቃድ  ወይም ያለፍድር ቤት ትእዛዝ እንደማይቆረጥበት ተደንግጎ ቢገኝም፣ መንግስት ግን ከሰራተኞች ላይ በግዳጅ እንዲቆረጠ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግስትን ድርጊት የተቃወሙ የመንግስት  ሰራተኞች ተቃውሞአቸውን በደብዳቤ እየገለጡ ቢሆንም፣ ከክልሉ የተሰጣቸው መልስ ግን እጅግ አስፈሪ ነው።

ተቃውሞአቸውን የገለጡ በርካታ ሰራተኞች፣ “ጸረ ሰላም ሀይሎች” የሚያስወሩትን በመስማት፣ ከጸረ ሰላም ሀይሎች ጋር እየተባበራችሁ ነው” የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ እየተላከላቸው ነው።

“ደሞዛችን ያለፍላጎታችን ለምን ይቆረጣል ብለን በመጠየቃችን ጸረ ሰላም ሀይሎች ተብለን ተወግዘናል” የሚሉት ሰራተኞች፣ ጸረ ሰላም ከሚለው ክስ ቀጥሎ እስር ሊከተል ይችላል በማለት ስጋታቸውን ገልጠዋል።

መንግስት ከሰራተኛው የሚነሳውን ተቃውሞ ስጋት ውስጥ ስለጣለው፣ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የግዳጅ መዋጮ እንዲቆም አድርጎ ነበር። አሁን ግን ያንን የግዳጅ መዋጮ ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ብዙ ሰራተኞችን እያበሳጨ ነው።

በቅርቡ እያንዳንዱ አርሶአደር ከ500 ብር ጀምሮ ለአባይ ግድብ መዋጮ እንዲከፍል ፣ መንግስት አዲስ ስልት መንደፉን መዘገባችን ይታወሳል።

ከኢትዮጵያ ባለፉት 7 አመታት  11 ቢሊዮን ብር ወደ ውጭ አገር መውጣቱ መዘገቡ ፣ የመንግስትን አመኔታ በእጅጉ እንደሚቀንሰው ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።