ህወሀት፤ የድርጅቱን ታሪክ በአዲስ መልክ ለማፃፍ 43 ሚሊዮን ብር መመደቡ ተጠቆመ

ህዳር 27 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የ “ከአገር በስተጀርባ”  መጽሐፍ  ደራሲን በመጥቀስ ፍኖተ-ነፃነት እንዳስነበበው፤የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑትን ዶክተር ሰሎሞን ዕንቋይን “ጠልመት” እና የ አቶ ሀይላይ ሀድጉ ሥራ የሆነውን “ንንዓት” የተባሉትን መጽሀፍት መሰረት በማድረግ፤ የህወሀትን ታሪክ በአዲስ መልክ  በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለማፃፍ 43 ሚሊዮን ብር ተመድቧል።

“የሀብት ብዛትና ስልጣን እውነተኛውን ታሪክ ሊቀይሩት አይችሉም” ያሉት የመጽሐፉ ደራሲ፤ “43 ሚሊዮን ብር ቀርቶ 43 ቢሊዮን ብር ቢመደብ ፤የህወሀት ሀጢአት ከቶ ሊሸፈን አይችልም”ብለዋል።

በተለየ መልኩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሀቶች መረጃና ምንጭ የማይገኝላቸውን አዳዲስ የፈጠራ ታሪኮችን  በብዛት በመጻፍና በመጽሀፍ መልክ በማሳተም ወደ ገበያ ማስገባት መጀመራቸው ይታወቃል።

ሰዎችም ሆነ ድርጅቶች አቅምና ጥንካሬ እያጡ ሲመጡና በራስ መተማመናቸው ሲጠፋ በታሪክ ውስጥ ወደመሸሸግ እንደሚያዘነብሉ አያሌ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ህወሐት የአማራውን የባህል ተጽኖ መከላከልና ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ መቆዬት የሚቻለው፣ የድርጀቱን ታሪክ እና የክልሉን ባህል በማስፋፋት ነው የሚል ፖሊሲ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ይታወቃል።

ህወሀቶች በቅርቡ የአጼ ሚኒሊክን ዝና ዝቅ የሚያደርግ ታሪክ ጽፈው አቅርበዋል።

እነ አቶ ስብሀት ነጋ የሚመሩት አዲስ ታሪክ የመፍጠር እንቅስቃሴ በህዝቡ ውስጥ ቅሬታ እየፈጠረ መምጣቱም ይታወቃል።

ጋዜጠኛ ፋሲል ሞገስ በአውራምባ ታይምስ ላይ ወጣቱ 10 አይነት የኢትዮጵያን ታሪክ እየተማረ መሆኑን እና ታሪኩም እርስ በርሱ እየተጋጨበት መምጣቱን ገልጾ መጻፉ ይታወቃል።