ሂውማን ራይትስ ወች የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ዙሪያ ያወጣውን መግለጫ ተቃወመ

መጋቢት ፲፭ (አሥራ አምስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ታዋቂው የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት የሆነው ሂውማን ራይትስ ወች ፣ ለአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ክፍል ሃላፊ ለሆኑት ፍሬዲሪካ ሞጋሪ በጻፈው ደብዳቤ፣ የህብረቱ ልኡካን ቡድን አባላት ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ያወጣው መግለጫ እጅዝ አሳዛኝ መሆኑን ገልጿል።
ህብረቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው አፈና ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ከአውሮፓ ህብረት ጋር በትብብር ለመስራት እንደማያስችል መግለጽ ነበረበት የሚለው የሂውማን ራይትስ ወች መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የሚታየው የሰብአዊ መብት አፈና ለስደተኞች መበራከት ምክንያት መሆኑን የህብረቱ አባላት ይገነዘቡታል ብሎአል።
በፈረንጆች አቆጣጠር ከህዳር 2015 ጀምሮ የገዢው ፓርቲ የጸጥታ ሃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ገድለው በ10 ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ማቁሰላቸውን ያስታወሰው የሰብአዊ መብት ድርጅቱ፣ በጥቅምት ወር የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአለማቀፍ ህግ የተፈቀዱትን ተቃውሞውን በሰላማዊ መንገድ የመግለጽ መብት እንኳን ያፈነነ ነው ብሎአል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ ከ20 ሺ በላይ ዜጎች መታሰራቸውን ፣ በሚዲያ እና በሲቪክ ማህበራት ተቋማት ላይ የተጣለው እገዳ መቀጠሉን፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች መታሰራቸውን የሚጠቅሰው ሂውማን ራይትስ ወች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማፈራረስ፣ መሪዎችን ማሰር፣ ከዚያ በሁዋላ ከቀሪዎቹ ጋር እንደራደር ብሎ መጋበዝ ትክክል አይደለም ሲል አክሏል።
እንደ ዶ/ር መረራ ጉዲና የመሳሰሉ ለዘብተኛ ነገር ግን ጠንካራ ተቃዋሚዎች በድርድሩ እንዲሳተፉ ለጠ/ሚኒስትሩ ሊነገራቸው ይገባ ነበር የሚለው ድርጅቱ፣ ያለ በቂ መረጃና ግንዛቤ አሁን ለሚደረገው የፖለቲካ ድርድር ድጋፍ መስጠት ፣ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት የሚበጀው አይደለም ሲል መክሯል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እየሆነ ባለበትና ለ18 ወራት የዘለቀው የሰብአዊ መብት ጥሰት በቀጠለበት ሰአት ስለኢኮኖሚ ትብብር ማውራት ተገቢ አለመሆኑንም ሂውማን ራይትስ ወች ገልጿል። በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ሊደረግ የታሰበው “ የቢዝነስ ፎረም” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስኪነሳ ድረስ እንዲራዘም ድርጅቱ ጠይቋል።
የአውሮፓ ፓርላማ እና የውጭ ጉዳይ ክፍል የሚያወጡዋቸው መግለጫዎች እርስ በርስ የሚጣሩ መሆናቸውን፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ፣ የፈለገውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ብትፈጽም፣ ከወዳጅ አገራት የሚደርስብህ ነገር የለም የሚል መልእክት እንደሚያስተላልፍ ድርጅቱ ገልጾ፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ጠቃሚ አጋር መሆኗ ባያጠያይቅም፣ ስለ ስደተኝነት፣ ልማትና ኢኮኖሚ እድገት ለማውራት ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሊኖራት ይገባል፣ ይህን ለማሳካት ደግሞ ሰብአዊ መብቶች ሊከበሩ ይገባል ብሎአል።
“ከዚህ በሁዋላ ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ስትገናኙ፣ በግልጽ ቋንቋ ዶ/ር መረራና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ፣ በህዝቡ ላይ ለተፈጸመው እልቂት አለማቀፍ መርማሪ አካል እንዲመረምር እንዲሁም በሚዲያና በሲቪል ሶሳይቲ ላይ የተጣለው ክልከላ እንዲነሳ እንድታሳስቡ” በአጽንኦት እንጠይቃለን ሲል መግለጫውን ደምድሟል።