ኢሳት (ኅዳር 23 ፥ 2009)
በቀጣዩ ወር በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነትና የኮሚሽነሮች ምርጫ ለኮሚሽነርነት እጩን አቅርባ የነበረችውን ኢትዮጵያ እራሷን አገለለች።
በሃምሌ ወር በሩዋንዳ ተካሄዶ በነበረው የህብረቱ የመጀመሪያ ዙር የምርጫ ሂደት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ካለው ስምንቱ የኮሚሽኑ ቦታዎች ለአንደኛው ተወዳዳሪን አቅርባ እንደነበር ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኮሚሽነርነት የተወዳደረበትን ቦታ ባይጠቅስም፣ በወቅቱ ለህብረቱ የጸጥታና የደህንነት ኮሚሽነርነት በርካታ ሃገራት ተወዳዳሪዎችን አቅርበው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
በሩዋንዳ ተካሄዶ በነበረው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሁሉንም ተወዳዳሪዎች በአባል ሃገራት ዘንድ በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ምክንያት ውድድሩ እንዲራዘም ተደርጎ በቀጣዩ ወር በአዲስ አበባ የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ወቅት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ይሁንና ለኮሚሽነርነት አንድ አጩን አቅርባ የነበረችው ኢትዮጵያ ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ ራሷን ከእጩነት አግልላለች። በቀጣዩ ወር በሚካሄደው በዚሁ የህብረቱ ምርጫ የሊቀመንበርነት ስልጣኑን ጨምሮ ለኮሚሽነርነት 41 እጩዎች ተፎካካሪ ሆነው መቅረባቸውን የአፍሪካ ህብረት ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ለሊቀመንበርነት እጩ ሆነው የቀረቡ ስድስት አጩዎች ከአንድ ሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ ክርክርን እንደሚያካሄዱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ቦትስዋና ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኬንያ ቻድና ሴነጋል ለኮሚሽኑ ሊቀመንበር ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ የሃገሪቱ ተወካዮች የሚያካሄዱት ክርክር አብላጫ ድምጽ ለማግኘት ይረዳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከወራት በፊት በሩዋንዳ ተካሄዶ በነበረው ምርጫ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡ ዕጩዎች የሚፈለገውን ድምጽ ሳያገኙ መቅረታቸው የሚታወስ ነው።
በቀጣዩ ወር በአዲስ አበባ በሚካሄደው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ወቅት ከ32 አመት በፊት ራሷን ከአባልነት አግልላ የነበረችው ሞሮኮ በድጋሚ አባል ሃገር ለመሆነ ያቀረበችው ጥያቄም ድምጽ ይሰጥበታል ተብሎ በአጀንዳ መያዙ ታውቋል።
የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሞሮኮ የራሴ ግዛት የምትላትን የአረብ ሰሃራዊ ሪፐብሊክ በአባልነት መቀበሉን በመቃወም ሃገሪቱ ራሷን አግልላ ቆይታለች። ይሁንና፣ ሞሮኮ የያዘችውን አቋም ስትቀይር ወደ ህብረቱ ለመመለስ የወሰነች ሲሆን፣ ከአባል ሃገራትም ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ስታደግ ቆይታለች።