አቶ ዳንኤል ሺበሺ ነጻ ተባሉ
ሐምሌ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከተፈቱ በሁዋላ ይግባኝ የተጠየቀባቸው የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ም/ል የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የደቡብ ክልል ተወካይ በመሆን ሲያገልግሉ የነበሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ፍርድ ቤት ዛሬ ነጻ ያላቸው ሲሆን፣ ሌላው ይግባኝ የተጠየቀባቸው የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ “ አስገራሚ በሆነ ውሳኔ” ከክሱ ነጻ ተብለዋል። በአቶ አብርሃ ላይ የተላለፈው የፍርድ ቤት ውሳኔ አስገራሚ የተባለው፣ ፖሊስ አቶ አብርሃ ደስታን ፈልጎ ለማቅረብ አለመቻሉን ከገለጸ በሁዋላ ነው። አቶ አብርሃ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ በእየለቱ እየጻፉና በመቀሌ ዩኒቨርስቲም እንደሚያስተምር እየታወቀ፣ ፖሊስ አድራሻቸውን ማወቅ አልቻልኩም በማለት ለፍርድ ቤት መናገሩና ውሳኔው በዚህ መልኩ መሰጠቱ የማህበራዊ ሚዲያው መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል። ፍርድ ቤቱም “ አቶ አብርሃ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብለትም፣ እንዲሁም ታስሮ እንዲቀርብ ትእዛዝ ቢሰጥም፣ ተከሳሹ መቅረብ ባለመቻሉ ክሱ ይቋረጥ” ብሎአል።
አቶ ዳንኤል ከኢሳት ጋዜጠኞች ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው በሸብር ወንጀል ቢከሰሱም፣ ለፍርድ ቤቱ “ እርሳቸውም የኢሳት ጋዜጠኞችም አሸባሪዎች አይደሉም” በማለት ተናግረው ነበር። ፍርድ ቤቱ አቶ ዳንኤል በሰላማዊ ትግል ፅኑ አቋም እንዳላቸው የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ማቅረቡን ገልጿል።
በድፍረቱና በበሳል አስተያየታቸው የሚታወቁት አቶ ዳንኤል፣ በአሁኑ ሰአት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል በሚል ሰበብ ከጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጋር በእስር ቤት ይገኛል። አቶ ዳንኤልና ጋዜጠኛ ኤልያስ በ50 ሺ ብር ዋስትና እንዲፈቱ የቦሌ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት ወሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።
በሌላ በኩል በልደታ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ምድብ ወንጀል ችሎት ፣ ወ/ሪት ንግስት ይርጋ በቤተሰቦቿ፣ በጠበቃ፣ በጓደኞች የሰዓት ገደብ ሳይደረግባት ማንኛዉም እስረኛ እንደሚጠየቀው እሷም እንድትጠየቅ የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል።
ወ/ት ንግስት በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባት እንዲሁም በቤተሰቦቿና ጓደኞቿ እንዳትጎበኝ ክልከላ መጣሉን በመግልጽ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርባ ነበር።