ጋምቤላ አሁንም በውጥረት ውስጥ ናት

ጥር 26 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጋምቤላ ክልል በምስጢር የደኅንነት አባል ሆነው ሢሰሩ  የነበሩት   አቶ ጌታቸው አንኮሬ  ባልታወቁ ሰዎች በድንገት ተገደሉ።

የ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ  እንደገለፀው፤ የደህንነቱ አባል መገደላቸውን ተከትሎ ቀደም ሲል በክልሉ የነበረው ውጥረት በከፍተኛ ደረጃ የተባባሰ ሲሆን፤የክልሉ ባለሥልጣናትና ካድሬዎችም ስጋት ላይ ወድቀዋል።

የህወሃት አባል በመሆን በክልሉ ለረዥም ዓመታት በምስጢር የደኅንነት ሠራተኛነታቸው የሚታወቁት አቶ ጌታቸው ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች  በተደጋጋሚ በጥይት ተደብድበው የተገደሉት፤ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በክልሉ  ፕሬዚዳንት በአቶ ኦሞት ኦባንግ መኖሪያ ቤት ውስጥ ስብሰባ ላይ ቆይተው ወደ  ቤታቸው ሲመለሱ ነው።

የደህንነት አባሉ ልክ የመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ እንደገቡ በጥይት መደብደባቸውን ያመለከተው የንቅናቄው መግለጫ፤ “በከተማዋ እምብርት ግድያውን ያከናወኑት ክፍሎች፤ ለምን ጥቃቱን እንደፈጸሙ ከየትኛውም ወገን በግልጽ የተነገረ ነገር የለም”ብሏል።

ከሰባት ዓመት በፊት ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች የክልሉን እስር ቤት ሰብረው በመግባት የፖሊስ ኮሚሽነሩን ዲድኦሞ ኦሙኒን በመግደል የሚፈልጓቸውን እስረኞች ማስፈታታቸው ከተነገረ ወዲህ፤ በጋምቤላ ከፍተኛ የደህንነት ሀላፊ ሲገደሉ አቶ ጌታቸው የመጀመሪያ ናቸው።

የንቅናቄው የመረጃ ምንጮች ግድያው በክልሉ በህወሀት አማካይነት እየተፈፀመ ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣና የመሬት ነጠቃና የግዳጅ ሰፈራ የፈጠረው እምቢተኝነት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ቢሆንም፤ እስካሁን ስለተወሰደው እርምጃ ሀላፊነቱን ወስዶ በግልጽ የተናገረ አካል የለም።

ግድያውን ተከትሎ የ አገዛዙ ታጣቂዎች፣ፌዴራል ፖሊሶችና ወታደሮች ገዳዮቹን አስሶ ለመያዝ በሚል እየተራወጡ እንደሚገኙና አምስት ሰዎችን በጥርጣሬ እንደያዙ ምንጮቹን በመጥቀስ የጠቆመው የንቅናቄው መግለጫ፤መረጃው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ስለገዳዮቹ ማንነት ምንም የተገኘ ፍንጭ አለመኖሩን አመልክቷል።

የአቶ ጌታቸውን ግድያ ተከትሎ በአካባቢው ውጥረቱ በመባባሱና ስጋቱ በማየሉ፤ የጋምቤላ ከተማ በወታደሮች ጥበቃ ስር እንድትሆን ትዕዛዝ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ የ ጥበቃ ሠራተኞች ግን ፕሬዚዳንቱ በቃል ያስተላለፉትን ይህን ትዕዛዝ በደብዳቤ ያረጋግጡልን በማለታቸው ለጊዜው ተጨማሪ የጦር ሀይል ሳይመደብ ቀርቷል።

ይኸው ካድሬዎችንና የአገዛዙን አገልጋዮች ጭንቀት ውስጥ የከተተው አደጋ በ ኦሞ ሸለቆ አበቦ አካባቢና በሌሎች ወረዳዎችም አለመረጋጋት በመፍጠሩ  ከበላይ አካል ለካድሬዎች፦”ማንንም አትመኑ!”የሚል መመሪያ መሰጠቱም ተሰምቷል።

በክልሉ እየጠፋ ያለው የሰው ህይወትና ንብረት፤እንዲሁም እየታዬ ያለው አለመረጋጋት እጅግ እንደሚያሣስበው የገለጸው የጋራ ንቅናቄው፤”ህዝብን አለማዳመጥ፣ ለህዝብ ፍላጎትና ውሳኔ አለመገዛት፣ዜጎችን እትብታቸው ከተቀበረበት መሬት በግዳጅ ማፈናቀል፣መሬታቸውን የመሸጥ ዘመቻ ማካሄድ የክልሉን ነዋሪዎችና መላውን የ ኢትዮጵያ ህዝብ ያሳዘነ በመሆኑ፤ለሚደርሰው ችግር ሁሉ ህወሀት/ኢህአዴግ ተጠያቂ ነው”ሲል አስታውቋል።

በሌላ ዜና ደግሞ በክልሉ አበቦ በሚባለው አካባቢ ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ የፌደራል ፖሊስ አባልና አንድ ሲቪል መገደላቸውን የጋምቤላ ወኪላችን ገልጧል። ሰዎቹ የተገደሉት በጋምቤላ በተካሄደው ግምገማ ሚስጢር አውጥታችሁዋል በሚል ምክንያት መሆኑን ዘጋቢያችን ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ ገልጧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሹፌርም ከስራው እንዲባረር ተደርጓል ተብሎአል። ሾፌሩ የተባረረው የፕሬዚዳንቱ ተላላኪ በመሆን ፕሬዚዳንቱ ህገ ወጥ ተግባራትን እንዲፈጽሙ አድርጎአል በሚል መክንያት ነው። አቶ መለስ ዜናዊ የክልሉ ፕሬዚዳንት የፈጸሙት ሙስናና ህገወጥ ተግባራት ከልክ በላይ ቢሆኑም፣ ከራሳቸው ደህንነት ጋር በተያያዘ ሊያባርሩዋቸው እንዳልፈለጉ ዘጋቢያችን አክሎ ገልጧል።