ደራሲ፣ ጋዜጠኛና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ አረፉ

የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-53 መፅሃፍትን ለህዝብ ያበረከቱት ታላቁ ደራሲ  ጋዜጠኛና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ  በ77 አመታቸውነው ያረፉት።

ደራሲ ማሞ ከጦርነት እና ከስለላ ጋር በተያያዘ የተረጎሙዋቸው ስራዎች በብዙ አንባቢያን ዘንድ እንዲወደዱ አድርጓቸዋል።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር  ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ የጤና ጥበቃው ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም  አንጋፋው ደራሲ ማሞ ውድነህ በጠና መታመማቸውን ተከትሎ የነፃ ህክምና የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ለሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥያቄ ከሳምንታት በላይ መልስ ሊያገኝ ባለመቻሉ ወቅሰዋቸው እንደነበር ይታወሳል።

የደራሲያን ማህበር ማሞ ውድነህ በነፃ እንዲታከሙ ለሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም የፃፈውን ደብዳቤ ራሳቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድረስ በመሄድ ለጸሀፊያቸው እንደሰጡ የገለፁት አቶ ጌታቸው፤ ጉዳዩ ግፊት እንዲደረግበት ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩም ተጨማሪ ደብዳቤ መፃፉን ጠቁመዋል።

“ያለምንም ማጋነን በየቀኑ  ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቢያንስ ሦስቴ አራቴ እንደውላለን፡፡ ክቡር ሚኒስትር  ደብዳቤውን አይተዋል ወይ?  ደራሲ ማሞ ውድነህ በአገራቸው ውስጥ የነፃ ሕክምና እንዲፈቀድላቸው ብለን ጠይቀናል፡፡ ምላሽ ግን አላገኘንም”ብለው ነበር ፕሬዚዳንቱ።

አቶ ጌታቸው አክለውም፦“ማኅበራችን እጅግ አዝኗል፤ ይቻላል አይቻልም አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላ አማራጭ እንዳንፈልግና  ወደ ሚረዷቸው ሰዎች እንዳንሄድ አድርገውናል፡፡ በመሠረቱ አቶ ማሞ ውድነህ በምንም ሆነ ምን አገራቸውን አገልግለዋል፤ በሙያቸውም፣ በአገር ሽማግሌነታቸውም  አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ለአገር የሚገባውን ሁሉ አድርገዋል” በማለት ለሪፖርተር መግለጣቸው አይዘነጋም።

ደራሲ ማሞ ውድነህ በበኩላቸው በተኙበት ሀኪም ቤት ተገኝቶ፦”ነፃ ህክምና ተፈቀደልዎት ወይ?” በማለት ሲጠየቁ፦”ለማን? ለእኔ? የት ያውቁኛል? ሚኒስትሩ አያውቁኝ፡፡መንግስት አያውቀኝ። ልጆቼን አውሎ ያግባልኝ። እስከዛሬ ያለው ደህና ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን አላውቀውም፤ ከበድ እያለ ይሄዳል”ሲሉ ሀዘናቸውንና ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።

ለአገራቸው አስተዋፅኦ ያበረከቱ ደራሲዎችንና የኪነ-ጥበብ ሰዎችን በመንከባከቡ ረገድ አፄ ሀይለሥላሴ በራቸው ክፍት ነበር ያሉት ደራሲ ማሞ ውድነህ፤ “ከእርሳቸው ወዲህ ምንም ነገር የለም”ሲሉ አክለው ነበር።

የኢሳት ዝግጅት ክፍል በደራሲ ማሞ ውድነህ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ለመግለጽ ይወዳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide