የጌዲዮ ተወላጆችና የዲላ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ ለሁለተኛ ጊዜ ታገደ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2011)የጌዲዮ ተወላጆችና የዲላ ነዋሪዎች በዲላ ሊያካሂዱት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ለሁለተኛ ጊዜ ተከለከለ።

በመጨረሻው  ሰአት ሰልፉ መከልከሉ እንዳሳዘናቸው አስተባባሪዎች ገለጹ።የዲላ ከተማ አስተዳደር ለሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች በላኩት ደብዳቤ ላይ ለህዝቡ ደህንነት ሲባል ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን ገልጸዋል።

የጌዲዮ ተወላጆችና የዲላ ነዋሪዎች በዲላ ሊያካሂዱት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ባለቀ ሰአት ሲከለከል ይሄ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ይላሉ የሰልፉ አስተባባሪዎች።ሰላማዊ ሰልፉ እንዲሳካ የሄዱበትን ርቀት በመግለጽም ጭምር

ለደህንነታችሁ ስጋት አለው በሚል የተከለከለውን ሰላማዊ ሰልፍ የጸጥታ ሃይልን አሰማርቶ ማስኬድ ሲቻል ሰልፉን ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘም ትክክል አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ከፌደራልና ከክልል ተልከው ባለቀ ሰአት ሰላማዊ ሰልፉ እንደማይካሄድ የነገሩን አካላት ምክንያትም ቢሆን አሳማኝ አይደለም ብለዋል።

የጸጥታ ችግር እንዳለበት ወደ ሚታወቀ ጨንቻ ተፈናቃዮችን እመልሳለሁ አካባቢውም ሰላም ነው የሚል አካል አሁን ደግሞ ዲላ ላይ የጸጥታ ችግር አለ የዜጎቼ ደህንነት ያሳስበኛል ሲል ሃሳቦቹ ይጋጫሉና ይሄንንም ቢያስተውል ጥሩ ነው ይላሉ።

ሰላማዊ ሰልፉ ሲደረግ የዲላ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ በዲላ ከተማ የሚገኙ ወገኖችም አብረውን ይሄን ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ከተማውን ከማጽዳት እስከ ባነሮችን መስቀል ብሎም ቲሸርቶችን አሳትሞ እስከማከፋፈል ያለውን ተግባር ሲያከናውኑ ነበር ብለዋል።

እንደዚህ አይነቱ ሰላማዊ ሰልፍ ሲታገድ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የሚሉት አስተባባሪዎቹ ሰላማዊ ሰልፉ ይታገድ እንጂ ከስራ ማቆም አድማ ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ የምናቀርበውን ጥያቄ ወፊትም እንቀጥላለን ብለዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሰላማዊ ሰልፉን ሊያደርግ በወጣው ህዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚችል የጸጥታ ችግር አለ በሚል ሰላማዊ ሰልፉን ማገዱን ነው ከከተማ ጽህፈት ቤቱ ከወጣው ደብዳቤ ማወቅ የተቻለው።

ኢሳትም መረጃውን ይዞ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወደ ተባሉት አካላት ያደረገው የስልክ ጥሪ ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም።