የጅግጅጋ ነዋሪዎች በቤተክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙና የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ጥረት ቢጀምሩም ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ተናገሩ

የጅግጅጋ ነዋሪዎች በቤተክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙና የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ጥረት ቢጀምሩም ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ተናገሩ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 03 ቀን 2010 ዓ/ም ) ኢሳት በስልክ ያነጋገራቸው የሶማሊ ክልል ተወላጆች በክልላቸው በተፈጠረው ድርጊት በእጅጉ እንዳሳዘናቸውና ድርጊቱም በጥቂት የአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች የተፈጸመ እንጅ የከተማዋን ነዋሪዎች እንደማይመለከት ገልጸዋል።
ጥቃት የተፈጸመባቸውን ወገኖች ቤታቸው አስጠልለው ያዳኑት አቶ ሽኔ፣ አቶ አብደ ኢሌ ቤተክርስቲያናትን ጨምሮ መቃጠል ያላበቸውን የንግድ ድርጅቶች ትዕዛዝ እየሰጠ እንዲወድሙ ማድረጉን ገልጸዋል። በአሁኑ ሰዓት እርሳቸውና ጓደኞቻቸው ተባብረው ድጋፍ ለማድረግ እየሞከሩ ቢሆንም፣ በከተማው በተፈጠረው የምግብና የውሃ እጥረት ምክንያት ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ገልጸዋል። የፌደራል መንግስት እስካሁን ድረስ እርዳታ ለማድረግ ባለመቻሉም ማዘናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው በክልሉ በተፈጸመው ድርጊት ህዝቡን አይወክልም የሚሉት አቶ አብዲ ሃሰን በበኩላቸው ዛሬ ጅግጅጋ ሰላም ቢሆንም፣ ለተቸገሩት ወገኖች እርዳታ አለመድረሱ ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል።
አቶ አብዲ ሙሃመድ በበኩላቸው ባዩትና በተፈጸመው ነገር ማፈራቸውን ተናግረዋል። ድርጊቱም ተወልደው ላደጉበት ከተማ ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ነው። እኛ በግል በቤተከርስቲያን ተጠልለው የሚገኙ ወገኖቻችንን ለመርዳት ሙከራ እያደረግን ነው የሚሉት አቶ አብዲ፣ አቶ አብዲ ኢሌን የተኩት ሃላፊዎችም እርዳታ ለማድረግ ዝግጁ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ሰመጉ ባወጣው መግለጫ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች አሁንም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ ብሎአል። በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጉና ገዶ ወረዳ ዱራሌ ተራራ አካባቢ የክልሉ ውሀ ቢሮ የሚያሰራው የውሀ መስመር ዝርጋታ ሠራተኞች የሆኑ 72 ዜጐች በአንዳንድ የአካባቢው ተወላጆች ዛቻ
እየተፈፀመባቸው መሆኑን እና ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ለሰመጉ በስልክ አሳውቀዋል፡፡
ሰመጉ አክሎም በድሬዳዋ ከተማ አንዲት እናት እና አራት ልጆቿን ጨምሮ 14 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል። አሁንም ይህ ሪፖርት በሚጠናቀርበት ጊዜ በድሬዳዋ ከተማ ታይዋንና አሸዋ ሰፈር በሚባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን የንግድ ሱቆችም መዘጋታቸውን ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ጠቅሷል።
የዜጐቹን ደህንነት የመጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት መንግስት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት በመስጠት የድርጊቱን ፈፃሚዎችና አስፈፃሚዎች በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፤ የህዝቡን ፍላጐት መሠረት ያደረገ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግ ጥሪ አቅርቧል። የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ህግን ለማስከበርና ስርዓትን ለማስፈን የሚወስዱት እርምጃ በከፍተኛ ጥንቃቄና የሀላፊነት ስሜት እንዲሁም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባከበረ መልኩ እንዲሆን ሰመጉ አሳስቧል።