የጁባ መንግስት በዋሽንግተን የሚገኙትን አምባሳደሩን ጠራ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2010)

አሜሪካ በደቡብ ሱዳን መንግስት ላይ የጣለችውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ተከትሎ የጁባ መንግስት በዋሽንግተን የሚገኙትን አምባሳደሩን መጥራቱ ተሰማ።

በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካና በደቡብ ሱዳን መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ያስከተለው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በደቡብ ሱዳን ያለውን ችግር ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተመልክቷል።

አሜሪካ በደቡብ ሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በደቡብ ሱዳን መንግስት ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጥል በወሩ መጀመሪያ ያቀረበችው እቅድ ሲከሽፍ ባለፈው አርብ በተናጠል የጦር መሳሪያ ማዕቀብ አድርጋለች።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃለይ “በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ማድረግ ቅጣት ሳይሆን የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ መታደግ ነው” በማለት ማዕቀብ እንዲጣል ያደረጉት ጥረት በሩሲያ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል።

ይህንን ተከትሎም አሜሪካ በተናጠል ባለፈው አርብ የጣለችው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የሱዳንን መንግስት አስከፍቷል።

ማዕቀቡን ተከትሎም በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙትን አምባሳደሯን ወደ ጁባ የጠራችው ደቡብ ሱዳን ርምጃው በማዕቀቡ ዙሪያ ከአምባሳደሯ ጋር ለመምከር እንደሆነ ገልጻለች።

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ጉዳዩን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት በማይጎዳ መልኩ እንመለከተዋለን ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 ነጻነቷን ያወጀችው ደቡብ ሱዳን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 በምክትል ፕሬዝዳንቱ ሬክ ማቻር ተሞከረ የተባለ መፈንቅለ መንግስትን ተከትሎ በቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

ውዝግቡን ለመፍታት በፕሬዝዳንት ሳልቫኬርና በአማጺው መሪ ሬክ ማቻር መካከል ወደ 11 ጊዜ የሰላም ስምምነት ቢፈረምም ግጭቱ ግን ሊቆም አልቻለም።

ወደ 4 ሚሊየን ከሚሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝብ አንድ አራተኛው መሰደዱ ሲገለጽ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰው እልቂት ከሶሪያው ፍጅት የማይተናነስ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል።