የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመድበው ገንዘብ ተቸገረ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2010)

በኢትዮጵያ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ተባብሶ በመቀጠሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኤምባሲዎችና ለቆንስላ ጽህፈት ቤቶች የሚመድበው ገንዘብ መቸገሩ ታወቀ።

ኤምባሲዎቹ እየገጠማቸው ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ በየሀገሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በኢንቨስትመንት ማበረታቻና በቤት መስሪያ ቦታ እያግባቡ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ቤት እንዲልኩ ታዘዋል።

ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ እየታየ ለኤምባሲዎቹ የበጀት ጉድለቱ እንደሚሸፈንላቸውም ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለሳምንታት ብቻ የሚበቃ እንደሆነ እየተገለጸ ባለበት በአሁኑ ወቅት መንግስት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በብድርና የውጭ ቦንድ በመግዛት ለመሸፈን የሚያደርገው ጥረት አልተሳካም።

የሚሰጠው ብድርም ይሁን እርዳታ በሀገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት የማይቀርፍ እጅግ አነስተኛ ሆኖ በመገኘቱ ከመድሃኒትና ነዳጅ ወጪዎች ባሻገር ሌሎች የወጭ ንግድ እቃዎችን ወደ ሀገር ቤት ለማስገባት ከፍተኛ ችግር መፈጠሩም ታውቋል።

ይህም በውጭ ሀገር ለሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች በውጭ ምንዛሪ የሚመደበው በጀትም ላይ ተጽእኖ በማድረጉ ነው ኤምባሲዎቹ የውጭ ምንዛሪ እንዲያሰባስቡ ጥሪ የተደረገላቸው።

ቤት በማህበርም ይሁን በግል መመራት የሚፈልጉ፣ በግልም ይሁን በማህበር ሕንጻ መገንባት ለሚፈልጉ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በቂ ቦታዎች አሉ በሚል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲመዘገቡና የቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍሉ የማግባባቱ ስራ ተጀምሯል።

ቤታቸውንም ሆነ ሕንጻቸውን ለመገንባትም ይሁን ለመጨረስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር እንደሚያመቻችም ለተመዝጋቢዎቹ እንዲነገር መመሪያ ተላልፏል።

ሀገሪቱ ካለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባሻገር አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ብር እንዳያትሙ የሰጠውን ማሳሰቢያ ተከትሎ የብር እጥረት በመኖሩ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችም በመቆማቸው ንግድ ባንክ ብድር ማመቻቸቱን ባለሙያዎች የማይታሰብ ሲሉ ይተቹታል።

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እየተባባሰ ከመቀጠሉ ጋር ተያይዞ የንግድ ሚዛኑ ይበልጥ እየተዛባ በመቀጠል ላይ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ።

ባለፉት 5 አመታት የታየው የንግድ ሚዛን መዛባት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩም ታውቋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የነበረው የንግድ ሚዛን ልዩነት በ2016 13 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።

ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተያዘበት በአሁኑ ወቅት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ቤት እንዳይልኩ የሚቀሰቅስና በባለሙያዎች የተቋቋመው ግብረ ሃይል በውጭ ሀገር ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

አለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የጋራ ግብረሃይል የተባለው የባለሙያዎች ቡድን የውጭ ምንዛሪ በህጋዊ መንገድ መላክ ሰርአቱን ስለሚያጠናክር ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም እንዲላክ ለማድረግ በመቀስቀስ ላይ ይገኛል።

ከተቻለ እንዲያውም ለተወሰኑ ወራቶች ጨርሶ አለመላክ ስርአቱን ይበልጥ ፈተና ውስጥ እንደሚጥለው ግብረሃይሉ ይገልጻል።