የዋጋ ግሽበቱ ወደ 18 ነጥብ 1 በመቶ አሻቀበ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 2/2010)

የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ወደ 18 ነጥብ 1 በመቶ ማሻቀቡን የማዕከላዊ ስታቲትክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የተጠናቀቀው ህዳር ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 13 ነጥብ 6 በመቶ እንደነበርም የኤጀንሲው መረጃ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ያለው የኑሮ ውድነት በቃላት መግለጽ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን መረጃዎች አመልክተዋል።

የማዕከላዊ ስታቲትክስ ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ ደግሞ አሁን ላይ የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ባለፈው ከነበረው እንኳን በ2 መቶ አሻቅቦ ታይቷል ይላል።

ኤጀንሲው እንደሚለው ከሆነ የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ወደ 18 ነጥብ 1 በመቶ አሻቅቧል።

ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ግሽበትም ቢሆን ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የኤጀንሲው መረጃ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ የህዳር ወር የዋጋ ግሽበት 13 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የነበረው የዋጋ ግሽበት 12 ነጥብ 2 እንደነበር የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ከተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ የነዳጅና የመድሃኒት መግዣ ዋጋ በእጅጉ ሊያሻቅብ እንደሚችልም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ የመድሃኒት እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መከሰቱም ታውቋል።

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ክምችት 700 ሚሊየን ዶላር ብቻ ሲቀር ይህ ደግሞ ለሶስት ሳምንት ብቻ የሚበቃ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።