የወሊሶ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የተቃውሞ አድማ እያደረጉ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 7/2011)ካምፕ የገባው የኦነግ ጦር ተመርዟል መባሉን በመቃወም በኦሮሚያ ክልል የወሊሶ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የተቃውሞ አድማ እያደረጉ ነው።

በአድማው ምክንያት ከወሊሶ ወደ አዲስ አበባ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ወሊሶ የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዳይገቡና እንዳይወጡ ወጣቶች መንገድ ዘግተዋል ተብሏል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ መግለጫ ያወጣው ኦነግ 200 የሚሆኑ የኦነግ ጦር አባላት የበሉት ምግብ የተበከለ በመሆኑ ለበሽታ መጋለጣቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ ከጦላይ ስልጠና ማዕከል በጤና ችግር ሆስፒታል የገቡ የኦነግ ሰራዊት አባላት በጥሩ ጤና ላይ የገናሉ ብሏል።

በወሊሶ ከተማ ያሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በአድማው ምክንያት አገልግሎታቸው ተቋርጧል

ጦላይ በሚገኘው ካምፕ የገቡ የኦነግ ጦር አባላት ተመርዘዋል መባሉን የተቃወሙ የወሊሶ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የተቃውሞ አድማ በማድረጋቸው የመንግሥት ተቋማትና ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል፡፡

ከመንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት ትጥቅ ፈትተው ወደ ጦላይ ካምፕ እንዲገቡ የተደረጉ የኦነግ ጦር አባላት ውስጥ ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑት በምግብ መመረዛቸው ታውቋል።

እናም ማለዳ ላይ ለተቃውሞ የወጡ የወሊሶ ወጣቶች የኦሮሚያ ክልልን በሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ላይ ያነጣጠሩ ወቀሳዎችን ሲሰነዝሩ ተሰምተዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ኦነግ መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም 200 የሚሆኑ የኦነግ ጦር አባላት የበሉት ምግብ የተበከለ በመሆኑ ለበሽታ መጋለጣቸውን አመላክቷል፡፡

ግንባሩ በመግለጫው ያጋጠመው ችግር በአስቸኳይ ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

በጦላይ የስልጠና ማዕከል በስልጠና ላይ ከሚገኙ የኦነግ ሰራዊት አባላት ጤና ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መግላጫ ሰጥቷል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው እንደገለጹት በትናንትናው እለት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ በጦላይ ስልጠና ማዕከል ውስጥ ያሉ የተወሰኑ የኦነግ ሰራዊት አባላት የጤና እክል ገጥሟቸው ሆስፒታል ገብተዋል።

በዚህ ስልጠና ማዕከል ከሚገኙ 1 ሺህ በላይ የኦነግ ሰራዊት ሰልጣኞች መካከል 136 ያህሉ በጋጠማቸው የጤና ችግር በወሊሶ ሉቃስ ሆስፒታል የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አግኝተው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በስልጠና ማዕከሉ የተከሰተው ይህ የጤና ችግር መንስኤም በመጣራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

የቢሮ ሃላፊው ትናንት ከተፈጠረው የጤና ችግር ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ያለፈና የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው የሰራዊት አባላት እንዳሉ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ሃሰት መሆናቸውን ተናግረዋል።