የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ 42 ኢትዮጵያዊያን በሳኡዲ አረቢያ ተደብድበው ታሰሩ

 

09 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-እንደ ቤተ ክርስቲያን በሚገለገሉበት የመኖሪያ ቤት ዉስጥ የምሽት ፀሎትና የሃይማኖት ትምህርት በመከታተል ላይ የነበሩ 42  የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያዊያን አሰሳ ባደረጉ የሳኡዲ አረቢያ የፀጥታ ሃይሎች ተይዘዉ መደብደባቸዉንና መታሰራቸዉን አለም አቀፍ የክርስቲያን ኮንሰርን ገልጧል።

የመረጃ ምንጩ እንደገለፀዉ ቁጥራቸዉ አናሳ የሆኑት የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እምነታቸዉን በነፃነት እንዳይከታተሉ በሳኡዲ አረቢያ ከፍተኛ ተፅእኖ አለባቸዉ።

በደቡብ ሳኡዲ አረቢያ ቀይ ባህር ጠረፍ ጂዳ ከተማ ፖሊሶችና የፀጥታ ሀይሎች በሃይል ሰብረዉ በመግባት የፈፀሙት ይህ ድብደባና እስራት የተፅእኖዉ አካል መሆኑ ታዉቋል።

በሳኡዲ አረቢያ ክርስያኖች ሊያመልኩ የሚችሉበት አንድ የቤተ ክርስቲያን ህንፃ እንደሌለና መንግስት ከዚህ አልፎ ዜጎችና የዉጭ አገር ተወላጅ የሆኑ ሰራተኞችን በየመኖሪያ ቤታቸዉ በግላቸዉ የሀይማኖት ነፃነት እንዳይኖራቸዉ በማደን ላይ እንደሚገኝ አይደን ክሌይ የአለም አቀፍ የክርስቲያን ኮንሰርን የመካከለኛዉ ምስራቅ ክልላዊ ስራ አስኪአጅ ገልፀዋል።

በማያያዝም ሳኡዲ አረቢያ የተባበሩት መንግስታት የፀረ ሰቆቃ ህግን አለም አቀፍ ድንጋጌ የፈረመች አገር እንደመሆኑዋ ፣  በኢትዮጵያዊያን የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ በእስር ቤት የሚፈፀምባቸዉ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲያቆምና እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

 የሳኡዲ ባለስልጣኖች ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ክርስቲያኖችን የሚያስር ቢሆንም እንደአሁኑ በገፍ ያደረገበት ጊዜ እንደሌለ የገለፁ አንድ በጄዳ ነዋሪ የሆኑ ክርስቲያን በበኩላቸዉ ፣ የታሰሩት ሰዎች ህፃናት ጉዳይ ይበልጥ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በአዉሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ስደተኞች በሪያድ ለሚኖሩ የአዉሮፓ ኤምባሲዎች ስለተፈፀመዉ ድርጊት ያላቸዉን ቅሬታ በመግለፅ አቤቱታ ማቅረባቸዉን አለም አቀፍ የክርስቲያን ኮንሰርን ገልጿል።

 በሳኡዲ አረቢያ በስራ ምክንያት የሚገኙ የዉጭ አገር ተወላጆች እምነታቸዉን በግልፅ ማካሄድ የሚከለከሉ ሲሆኑ የሳኡዲ ፖሊሶች በየቤቱ አሰሳ በማድረግ የሚያገኟቸዉን እንደሚያስሩ፤ ከአገር እንደሚያባርሩና የሚያገኙትን መፅሃፍ ቅዱስ የመሳሰሉ ንብረቶችን እንደሚወርሱ አለም አቀፍ የክርስቲያን ኮንሰርን ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመላዉ አለም የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ከፍተኛዉን ቁጥር እንደያዙና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ሲ ኤን ኤን ዘገበ። 

እኤአ በ2010 በነበረዉ 6.9 ቢሊዮን ከሚሆነዉ የአለም ህዝብ ዉስጥ 2.2 ቢሊዮን የሚሆኑት የክርስትና፤ 1.6 ቢሊዮን የሚሆኑት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መሆናቸዉን መሰረቱን በዋሺንግተን ያደረገዉ ፒዉ ፎረም ኦን ሪሊጂን ኤንድ ፐብሊክ ላይፍ የተሰኘዉን ድርጅት በመጥቀስ ሲ ኤን ኤን ገልጿል። 

በመላዉ አለም የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ከፍተኛ ቁጥር ካላቸዉ 10 አገሮች መካከል ዩናየትድ ስቴትስ፤ ብራዚልና ሜክሲኮ የመሪነቱን ስፍራ ይዘዋል።

ከአጠቃላዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ግማሽ የሚሆኑት የካቶሊክ፤ 37 በመቶ የፕሮቴስታንት፤ 12 በመቶ የሚሆኑት የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ሲሆኑ ፣ አንድ በመቶ የሚሆኑት ሞርሞኒዝም የተሰኘዉ እጅግ ጥንታዊ የሆነዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ሲ ኤን ኤን አመልክቷል።