የኪርጊስታን ወታደራዊ አውሮፕላን በደረሰበት ቃጠሎ 15 ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 6/2011) ንብረትነቱ የኪርጊስታን መንግስት የሆነ የዕቃ ማጓጓዣ ወታደራዊ አውሮፕላን በደረሰበት ቃጠሎ 15 ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ።

ቦይንግ 707 የሆነው ወታደራዊ አውሮፕላን አሳፍሯቸው ከነበሩት 16 ሰዎች በህይወት የተረፈው አንድ ሰው ብቻ ሲሆን እሱም ሆስፒታል መወሰዱ ተመልክቷል።

በመጥፎ አየር ጸባይ ሳቢያ ዛሬ በአራን ርዕሰ መዲና ቴህራን አቅራቢያ ፍታህ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲሞክር መንደርደሪያውን በመሳቱ ቃጠሎ የደረሰበት ይህ ቦይንግ 707 ወታደራዊ አውሮፕላን ንብረትነቱ የኪርጊስታን መንግስት እንደሆነም ተመልክቷል።

ቅድሚያ የወጡ ሪፖርቶች አውሮፕላኑ ንብረትነቱ የኢራን እንደሆነ የተገለጸ ቢሆንም የኢራን መንግስት አውሮፕላኑ የኪርጊስታን መንግስት መሆኑን ገልጿል።

ስጋ ጭኖ ክርኪርጊስታን ርዕሰ መዲና ቢሸኮክ የተነሳው ይህ አውሮፕላን የደረሰበት ቃጠሎ መንስኤ እየተጣራ መሆኑም ተመልክቷል።

አደጋው በመጥፎ አየር ጸባይ ሳቢያ መሆኑ ቢገለጽም ተጨማሪ ምርመራ ይደረጋል ተብሏል።