የኤርትራ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሊሄድ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 29/2011)የኢትዮጵያና የኤርትራን ወዳጅነት ለማጠናከር ያለመ የኤርትራ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት ኢትዮጵያ እንደሚገባ ኤርትራ አስታወቀች።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በድረ ገጹ እንደገለጸው ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዘው የልኡካን ቡድን ታዋቂ የኤርትራ ሙዚቀኞችን ቡድን አካቷል።

ይሄ የሙዚቀኞች ቡድን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሙዚቃ ኮንሰርት እንደሚያቀርብም ተመልክቷል።

ታዋቂ የኤርትራ የሙዚቃ ባለሙያዎችን ያካተተ ነው የተባለው የኤርትራ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት ዝግጅቱን በባህርዳር እንደሚጀምርም ታውቋል።

ከዚያም ከባህርዳር ወደ አዳማ በመጓዝ ተመሳሳይ የሙዚቃ ዝግጅት ያቀርባል ተብሏል።

በቀጣይም በሐዋሳና በአዲስ አበባም ይህው መርሃ ግብር እንደሚቀጥልም ከኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መግለጫ መረዳት ተችሏል።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የኤርትራ ታዋቂ ሙዚቀኞች ዝግጅታቸውን የሚያቀርቡት ከኢትዮጵያ ታዋቂ ዘፋኞች ጋር በጋራ መሆኑንም ይፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከግንቦት ወር 1990 ጀምሮ በጦርነትና በውዝግብ ውስጥ ማለፋቸው ይታወሳል።

የ20 አመቱ ቅራኔና የጠላትነት ስሜት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ መሻሻሉና ወደ አዲስ ምዕራፍ መሻገሩ ይታወሳል።