የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች በኦጋዴን 16 ሰላማዊ ዜጎችን መግደላቸዉ ተገለፀ

የካቲት 9 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በደቡብ ምስራቅ ኦጋዴን በደገሃቡር ጉነ-ጋዶ አካባቢ የኢትዮጵያ መንግሰት ወታደሮች በመንገድ ዳር ሰብሰብ ብለዉ ይነጋገሩ በነበሩ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ 16 ሰዎች መግደላቸዉን የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር መግለፁን ብሉምበርግ የዜና ወኪል ገልጿል።
በወቅቱ ነዋሪዎቹ በመነጋገር ላይ የነበሩት ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ በአካባቢዉ ነዋሪ በሆኑ አንድ አረጋዊና አንድ የፖሊስ ኮሚሽነር ላይ ስለተፈፀመዉ ግድያ እንደነበር የዜና ምንጩ በተጨማሪ ገልጿል።
በተጨማሪ የመንግሰት ወታደሮች ከ100 በላይ የአካባቢዉን ነዋሪዎች አስረዉ ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸዉን አማፅያኑ መግለፃቸዉን አስታዉቋል።
ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ ብሉምበርግ የዜና ወኪል ለኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ በረከት ስምዖን በእጅ ስልካቸዉ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግም መልስ ሊያገኝ እንዳልቻለ ገልጿል።