የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅነት የውጭ ሃይሎችን ምኞት ያመከነ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 26/2011) በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላምና የተከተለው ወዳጅነት የውጭ ሃይሎች ቀጠናውን ለመቆጣጠር የነበራቸውን ምኞት ያመከነ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ገለጹ።

በሌላም በኩል በኤርትራ ላይ ለአመታት ተጭኖ የነበረውን ማዕቀብ ለማንሳት እንቅስቃሴ መጀመሩም ተመልክቷል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቄ በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ ጥቅምት 24/2011 ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከኢትዮጵያ ጋር የተደርገው የሰላም ስምምነት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ለቀጠናው ትብብር ያደረገውንም አስተዋጽኦ ዘርዝረዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው ስምምነት የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በመቀበል ዙሪያ የተገደበ ሳይሆን ከዚያ ያለፈ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

የኤርትራም ሕዝብ ለአመታት ችግርን በጽናት ተጋፍጦ በመጨረሻ ለድል በቅቷል ሲሉም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በቀጠናው የትብብር እንቅስቃሴዎች በመጠናከር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ፣ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች አስመራ ላይ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ጅቡቲንም የሒደቱ አካል ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም መረጃዎች አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ፣ኤርትራና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ጅቡቲ ተጉዘው የጅቡቲውን ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌን አነጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በቅርቡ ወደ አውሮፓ ባደረጉት ጉዞ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠታቸውም ይታወሳል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኤርትራና ጅቡቲ ጉዳይ ላይ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ፈረንሳይ የጅቡቲ ቅኝ ገዥ የነበረችና አሁንም በሃገሪቱ የጦር ሰፈር ያላት ሃገር ናት።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በኢትዮጵያ መንግስት ግፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2009 ጀምሮ ላለፉት 10 አመታት ያህል በኤርትራ ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ ሊነሳ መሆኑ ተገልጿል።

ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኢጋድ እንዲሁም አፍሪካ ሕብረትን በማግባባት ጉዳዩን በመግፋታቸውና አሜሪካም በመቀበሏ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በታህሳስ ወር 2009 በኤርትራ ላይ የጦር መሳሪያና የጉዞ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

በኤርትራ ላይ ለ10 አመታት ያህል የዘለቀው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲሁም በመሪዎቿ ላይ የተጣለው የጉዞ ማዕቀብና ሃብታቸው እንዳይንቀሳቀስ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ በቅድሚያ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሲሆኑ ሌሎች ሃገራትም ድጋፍ በመስጠታቸው ማዕቀቡ ሊነሳ መሆኑ ተመልክቷል።

አሜሪካም በማዕቀቡ መነሳት ላይ ፍላጎቷን በማሳየቷ በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ማዕቀቡን ለማንሳት የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በኤርትራ ላይ ማዕቀቡን ለማንሳት መነሻ ሆኖ የቀረበው የሶማሊያውን አሸባሪ ሃይል አልሻባብን ትረዳለች በሚል ሲሆን የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት ኽርማን ኮህን እንደገለጹት ለዚህ የቀረበ አንድም ማስረጃ የለም።