“የኢህአዴግ ስርዓተ-መንግስት ሳይውል ሳይድር በዲሞክራሲያዊ ስርዓት መተካት አለበት” ሲል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዶሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ገለፀ

ኢሳት ዜና:- መድረክ ይህን ያለው፦ “በኢትዮጵያ ድርቅ አለ፤ ረሀብም አለ፤ ኢኮኖሚውም መንግስት እንደሚለው እያደገ አይደለም። የፖለቲካ ምህዳሩም ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠቧል” በሚል ርዕስ ትናንት ባወጣው ባለ ስምንት ገፅ መግለጫ ላይ ነው።

ፕሬዚዳንት ግርማና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለፓርላማ ባቀረቡት  የአዲስ አመት ንግግር ሰፋፊ ዲስኩሮችን አስደምጠውናል ያለው መድረክ፤በንግራቸው የነካኳቸው ጉዳዮች ብዙ ቢሆኑም በሁሉም ዘርፎች ያሏቸው ነገሮች ስህተት እንደሆኑ መረጃዎችን በመጥቀስ አብራርቷል።

በአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ሳይንሳዊ ትንታኔ መሰረት “ረሀብ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ በስፋት ያብራራው መድረክ፤ ”ይህን ሳይንሳዊ እውነታ “አንድም በረሀብ የሞተ ሰው የለም” ከሚለውና ሀላፊነት ከጎደለው የመንግስት አባባል ጋር ስናስተያየው፤ በኑሮ ምቾት የናወዙ የመንግስት ባለስልጣናትን ማንነት መገንዘብ ይቻላል”ብሏል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል ”በረሀብ አንድም ሰው አልሞተም” ማለታቸውና አሁን ደግሞ አቶ መለስ በፓርላማው ” የእርዳታ እህል መምጣት የጀመረው ሱማሌ ክልል ውስጥ ሰው
መሞት ሲጀምር ነው” ማለታቸው፤ እርስበርሱ የሚጣረስ መሆኑንም  መድረክ አመልክቷል።

ሌሎች ባለስልጣኖች ብዙ ርቀት ሄደው ለመዋሸት እየፈለጉ በራሳቸው በአቶ መለስ ሲዋረዱ አቶ ሀይለማርያም የመጀመሪያ አይደሉም።

ቀደም ሲል አቶ ሽመልስ ከማል “የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮን  የኢትዮጵያ መንግስት ጃም አላደረገም” የሚል መግለጫ በሰጡበት ማግስት አቶ መለስ ”ጃም አድርገነዋል”
ብለው መናገራቸው አይዘነጋም።

“በሀገራችን ውስጥ በተከሰተው የረሀብ ጉዳይ ላይ መረጃና ማስረጃ ይቅረብ ከተባለ የመረጃው ምንጭ የችግሩ ሰለባ እየሆነ ያለው ህዝባችን ነው” ያለው
መድረክ፤ ይህ ትክክለኛ ማስረጃ ሊገኝ የሚችለው በየአካባቢው ልማትን አስፋፍቻለሁ እያለ ለሹመትና ሽልማት ከሚሽቀዳደመው ሞራለ-ቢስና ሆድ አደር የኢህአዴግ ካድሬ አይደለም” ብላል።

አክሎም፦”ስነ-ምግባር አልባው ካድሬማ ከለጋሾች የሚገኘውን እርዳታ ሸጦ ከመብላት አልፎ የተረፈውንም በረሀብ የተመቱ ዜጎችን በኢህአዴግ ደጋፊነትና ተቃዋሚነት በመፈረጅ እየፈፀመ ያለው የክፍፍል አድሏዊነት ወንጀል ገሀድ የወጣ ነው” ሲል ነቅፏል።

ከዚህም በላይ’ የተራቡ ሰዎች በ አሜሪካም፤በ አውሮፓም አሉ” በማለት ሊወዳደሩ የማይችሉ ነገሮችን በማወዳደር በተራበው ህዝባችንና መጠለያ አጥቶ በየሜዳው በወደቀው ዜጋችን ላይ እያላገጠ ነው ያሉውን የአቶ መለስን አስተዳደር ”ጨካኝ መንግስት” ሲል ገልፆታል የመድረክ መግለጫ።

አቶ መለስ እያስመዘግብን ነው የሚሉት የኢኮኖሚ ዕድገት ፈፅሞ ስህተት እንደሆነ፤የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ፤ ህዝብን የማይጨበጥ ተስፋ በመመገብ ጊዜን ከመግዛት  አልፎ ጠብ የሚለው ነገር እንደማይታይበት፤ ለውጭ ባለሀብቶች በነፃ ሊባል በሚችል ዋጋ እየተሰጠ ባለው ሰፋፊ መሬት፤ አገሪቷና ህዝቦቿ ከፍ ያለ አደጋ ውስጥ እየወደቁ እንደሚገኙ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በመንተራስ መድረክ በስፋት
አመልክቷል።

በቅርቡ የይስሙላ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው የታሰሩት የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ጋዜጠኞች አራት ወር ቢያልፋቸውም ገና ማስረጃዎችን እያሰባሰብን ነው እየተባለ ጉዳያቸው ለፍርድ ቤት አለመቅረቡ፤ኢህአዴግ ያሰራቸው ማስረጃ ኖሮት ሳይሆን፤ ካሰራቸው በሁዋላ ወንጀለኛ የሚያሰኝ ማስረጃ እየሰበሰበ እንደሆነ ለማንም ግልጽ መሆኑን መድረክ አትቷል።ኢህአዴግ ራሱ ከሳሽ፤ ራሱ አስመስካሪ፤ ራሱ መስካሪና ራሱ ዳኛ በሆነበት የፍትህ ሂደት ደግሞ አንድን ንፁህ ዜጋ ከሶ “ወንጀለኛ ማሰኘት እንደማያቅተው የጠቀሰው መድረክ ፤”ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለይስሙላ እንኳ የፍርድ ቤትን ክርክርና ውሳኔ ሳይጠብቁ ተከሳሾቹን “አሸባሪ” በማለት የፈረጇቸው፡፤ይህ ቅድመ-ፍርድ ቤት አቋማቸው ደግሞ ፍርድ ቤቱ ከሳቸው ቃል እንደማይወጣ የሚያመለክት ነው”ብሏል።

አቶ መለስ በፓርላማ ንግግራቸው ሙስናን ስለመዋጋትና መልካም አስተዳደር ስለማስፈን ማውሳታቸውን የጠቀሰው መድረክ፦”የምክር ቤትም ሆነ የኢህአዴግ ስበሰባዎች በተካሄዱ ቁጥር ሙስናን ከምንጩ እናደርቀዋለን፤ ብልሹ አስተዳደርን እንመነግላለን “ያልተባለበት አጋጣሚ እንደሌለ በመጥቀስ፤ በተግባር ግን ችግሮቹ ሲባባሱ እንጂ ሲቃለሉ አለመታየታቸውን አመልክቷል።

“አሁንም ያው የተለመደ ተስፋ ቢሰጥም፤ የዓሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ” እንደሚባለው፤ለተንሰራፋው ሙስና ዋና አራማጆች የኢህአዴግ አመራሮች፤ ሹማምንቶቻቸውና የውሸት መፈክር እያስተጋቡ ያሉት ካድሬዎቻቸው
ናቸው። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ያርማሉ ማለት ዘበት ነው” ሲል የአቶ መለል ቃል ባዶ ተስፋ መሆኑን ጠቁሟል።

መድረክ አያይዞም ”የብልሹ አስተዳደር አራማጆችም እነዚህ በዘመድ አዝማድና በአካባቢ ልጅነት የሚሠሩ ሰዎች ናቸው። ደጋግመውን እንዳልነው፤ ሙስና ራሱን መታገል አይችልም።ብልሹ አሰተዳደርም ራሱን መታገል አይችልም።ሙስናና ብልሹ አስተዳደር ሊወገዱ የሚችሉት፤ እውነተኛ ዲሞክራሲ ሲሰፍን፣ዚጎች በነፃነት ማሰብና መደራጀት ሲችሉና የህግ የበላይነት ሲከበር ነው።ኢህአዴግ፤ የነዚህ ሁሉ ፀር እንጂ፤ አራማጅ አርቲ ሊሆን አልቻለም” ብሏል።

መድረክ በመጨረሻም “ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህን ማረጋገጥና የዜጎችን ክብር ማስጠበቅ አቅቶታል።ስለሆነም ነው የኢህአዴግ ስርዓተ-መንግስት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሳይውል ሳይድር መተካት አለበት የምንለው። የኢትዮጵያ
ህዝብና የኢህአዴግ አባለት ጭምር መገንዘብ ያለባቸው፤ በሀገራችን ስር እየሰደደ ላለው ችግር ተጠያቂው ኢህአዴግ እንጂ ተቃዋሚዎች አለመሆናቸውን ነው” ብሏል።