የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከነገ ጀምሮ እንደሚሰበሰብ ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2011)የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚሰበሰብ አስታወቀ።

በአባል ድርጅቶቹ በተለይም በሕወሃትና በሌሎች መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ግዜ እየሻከረ በመጣበት ወቅት የተጠራው ይህ ስብሰባ በፌደራል መንግስት በከባድ ወንጀል የሚፈለጉትን አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን የትግራይ ክልል መንግስት የደበቀበትን ጉዳይ ጨምሮ በርካታ የልዩነት ነጥቦች ይነሱበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ስፍራውን ለአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለማሸጋገር የተንቀሳቀሱት የሕዉሃት መሪዎች የቀድሞው ተሰሚነታቸውና ተጽዕኗቸው ባለመኖሩ ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ እንደነበሩ በወቅቱም ተዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሃላ መፈጸማቸውን ተከትሎ በተወሰዱ ርምጃዎችም የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች ደስተኛ አልሆኑም።

የፖለቲካ እስረኞች በተለይም የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና የኮለኔል ደመቀ ዘውዱ መፈታት ያላስደሰታቸው የህዉሃት መሪዎች ለ27 ዓመታት ጠቅልለው ይዘውት በነበረው የሃገሪቱ የስልጣን ቦታ ላይ ሽግሽግ ሲደረግም ርምጃውን በሕዉሃት እና በትግራይ ህዝብ ላይ የተከፈተ ጦርነት አድርገው በመመልከት ሲቀሰቅሱበት ቆይተዋል።

ሰኔ 16 ቀን 2010 በአዲስ አበባ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በመግደል የፖለቲካ ስልጣኑን መልሶ ለመቆጣጠር የቦምብ ጥቃቱን በዋናነት ያቀነባበሩት የቀድሞው የደህንነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ መሆናቸውንም አቃቤ ህግ ይፋ አድርጓል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ ከግንቦት ወር 1993 ጀምሮ በሃላፊነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ በሃገሪቱ ዜጎች ላይ ለፈጸሙት ሰቆቃ እንዲሁም ከለውጡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ግድያን በማቀነባበር በተጠረጠሩበት ወንጀል የእስር ትዕዛዝ ቢወጣባቸውም የትግራይ ክልል መንግስት አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ አቶ ጌታቸው ዛሬም ትግራይ ውስጥ መደበቃቸው ታውቋል።

እንዲያውም የትግራይ ክልል የጸጥታ አማካሪ ሆነው መሾማቸውም ይፋ ሆኗል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ የሕዉሃትና ኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ቢሆኑም እታሰራለሁ በሚል ፍርሃት አዋሳ ላይ በተካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ እንዳልተገኙ ይታወቃል።

አሁን አዲስ አበባ ላይ በተጠራውና ነገ በሚጀመረው ስብሰባም እንደማይገኙ ታምኖበታል።