የኢህአዴግ መንግስት የሙስሊሙን ማህበረሰብ ከሁለት መክፈሉንና አክራሪ ያላቸውን ወገኖች በማሳደድ ላይ መሆኑን ሙስሊሞች ተናገሩ

ኢሳት ዜና:- የኢሳት ዘጋቢ ያነጋገራቸው ሙስሊሞች እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ መንግስት አንዱን ወገን አህባሽ ሌላውን ወገን ደግሞ ዋህቢ በማለት መከፋፈሉ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ቅሬታን ፈጥሯል። ክፍፍሉን ተከትሎም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ለእስር ተዳርገዋል። በአዲስ ዘመን ከተማ ደግሞ የወረዳው የእስልምና ሀላፊ የነበሩት በታጣቂዎች መገደላቸው ታውቋል።
መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ቀርጾና በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አህባሽን እንዲከተል የማስገደዱን እርምጃ የተቃወሙ በርካታ የሀይማኖቱ ኡላማዎች ለስግደት ወደ ሳውዲ አረቢያ ከሄዱበት እንደማይመለሱ የደረሰን መረጃ አመልክቷል። እንድ ስሙ እንዳይገለጥ የፈለገ ሙስሊም እንዳለው በአሁኑ ጊዜ በሙስሊሙ ማህበረሰብና በመንግስት መካከል ከፍተኛ የሆነ ውጥረት አለ። ሙስሊሙ ማህበረሰብ በነጻነት እምነቱን ሲከታተል በአዲሱ የጸረ ሽብር አዋጅ አክራሪ ተብሎ ይታሰራል ብሎአል::
መንግስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የነፍጠኛው መሸሸጊያ ሆናለች በማለት በውስጥ ችግር እንድታመስና እንድትዳከም ካደረገ በሁዋላ አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ እስልምና ተከታዮች ማዞሩን አስተያየት ሰጪዎችን በመጥቀስ ዘጋቢያችን ገልጧል። በምርጫ 97 ወቅት ኢህአዴግ የሙስሊሙ ጠበቃ ነው በማለት ቅስቀሳ ማድረጉን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ አሁን ደግሞ የሀይማኖቱን ተከታዮች ለሁለት ከፍሎ እርስ በርስ እንዲጋጩ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን እነዚሁ ግለሰቦች ተናግረዋል።
አህባሽ የተባለው የእስልምና አስተምህሮ በኢትዮጵያዊ ሊባኖሳዊ ዜጋ አማካኝነት መጀመሩን መዘገባችን ይታወቃል። በኢትዮጵያ በሀይማኖቶች መካከል ለዘመናት የነበረው መቻቻል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ በሆዱ አገሪቱን ሊፈነዳ በተቃረበ የእስተገሞራ አለት ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል ሲሉ አስተያየታቸውን ለዘጋቢያችን የሰጡ ኢትዮጵያውያን አስተረድተዋል። ገዢው ፓርቲ ለስልጣን ማራዘሚያ ሲል የሚከተለው አደገኛ ፖሊሲ፣ በአገሪቱ ውስጥ ለሚፈጠረው የሀይማኖት ግጭት ተጠያቂ ይሆናል በማለት አክለዋል።