የአፋር ህዝብ ፓርቲ በአፋር ክልል በውጭ አገር ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አወገዘ፣ የመንግስት እጅ ሳይኖርበት እንደመማይቀርም ገለጠ

ጥር 9 ቀን 2004 ዓ/ም

ት ዜና:-የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ ለኢሳት እንደተናገሩት  በውጭ አገር ዜጎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ ፓርቲያቸው ያወግዘዋል።

በኦጋዴን ክልል የኢትዮጵያ መንግስት በ9 ቻይናውያን እና ከ60 በላይ ኢትዮጵያውያን ከ4 አመታት በፊት የተፈጸመውን ግድያ ምክንያት በማድረግ እስከዛሬ ድረስ አካባቢውን የጦር ቀጠና ማድረጉ ይታወቃል።

በሰሞኑ ጥቃት 5 የጀርመን፣ የሀንጋሪና ኦስትሪያ ዜጎች ሲገደሉ፣ ሁለት የጀርመን፣ እንድ የኦስትሪያና ሁለት የኢትዮጵያ ታጣቂዎች ደግሞ ተይዘው ተወስደዋል።

አቶ በረከት ስምኦን ድርጊቱን የፈጸሙት በኤርትራ የሚደገፉ የአፋር አማጽያን ናቸው ይላሉ። የኤርትራ መንግስት የአፍሪካ ህብረት ተወካይ የሆኑት   አምባሳደር ግርማ አስመሮም የኢትዮጵያን መግለጫ የፈጠራ ክስ በማለት አስተባብለዋል።

አምባሳደሩ ” ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በተቃረበ ቁጥር እንዲህ አይነት ስሜት የሚነኩ ዘገባዎችን በማቅረብ ባህሪ አድርጋዋለች ” ሲሉ ተችተዋል።

አፍሪካ ህብረት ስብሰባ በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ከሁለት አመት በፊት በነበረው የእፍሪካ ህብረት ጉባኤ ሳምንት ኢትዮጵያ ኤርትራ አዲስ አበባን ባግዳድ ለማድረግ አቅዳለች በማለት ክስ አሰምቶ ነበር።

አሁንም ተመሳሳይ ክስ በኢትዮጵያ በኩል መቅረቡና ችግሮች ሁሉ ተከሰቱ የሚባለው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ሲቃረብ መሆኑ ሆን ተብሎ የተደረገ ይሁን በድንገት የቀረበ የታወቀ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ ሰላም ሰፍኗል እያለ ዘወትር ቢናገርም፣ በአፋር እና በኦጋዴን እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ ጠረፋማ ቦታዎች በነጻነት መንቀሳቀስ አይቻልም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የውጭ አገር ቱሪስቶችን ግድያ አስመልክቶ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ አስተያየቶችን በድረገጾች እየሰጡ ነው።

የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ከኤርትራ ጋር ጦርነት እንዲካሄድ ሲወተውቱ፣ ሌሎች ደግሞ ይህን የፈጸመው የኢትዮጵያ መንግስት ነው ይላሉ። በተለይም መንግስት በቅርቡ አኬል ዳማ የሚል ድራማ መስራቱ እና ተቀባይነት ማጣቱ አሁንም የሽብር ጥቃት አደጋ መኖሩን ለማሳየት ብሎ የፈጸመው  ሊሆን እንደሚችል አስተያየቶች ቀርበዋል።