የአንድ አማራ ድርጅት አዲሱን የፖለቲካ ድርጅቱን አስተዋወቀ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 18/2010)በአማሮች ላይ ላለፉት 27 አመታት በተደራጀ መንገድ ሲካሄድ የነበረውን ጥቃት ለመከላከልና የአማራውን ሕልውና ለማስጠበቅ “በአንድ አማራ” ስር ተደራጅተናል ያሉ ኢትዮጵያውያን አዲሱን የፖለቲካ ድርጅታቸውን በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስተዋወቁ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩና በመአሕድ አባልነትና አመራር ውስጥ ጭምር ማለፋቸው የተገለጸው የአዲሱ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች በሃገር ውስጥ የሚደርገውን ትግል ለማገዝና የአማራውን ሕልውና ለማስጠበቅ መነሳታቸውን ገልጸዋል።    “የአንድ አማራ” ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ንጉሴ አዳሙ እንዲሁም ሌሎቹ የአመራር አባላት አቶ ሃይለገብርኤል አያሌው፣አቶ ዳንኤል ሃይሌና አቶ ቦጋለ አሰፋ በተገኙበት ድርጅቱ በዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ ሲልቨር ስፕሪንግ ከተማ ባለፈው ቅዳሜ በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ሒደቱን በማገዝና በማመቻቸት አስተዋጽኦ ያደረጉት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስና ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው በስነስርአቱ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን ትግል ለማቀናጀትና የአማራ ድርጅቶችን ወደ አንድ ለማሰባሰብ የተደረገውን ሙከራ አስታውሰዋል።

የአንድ አማራ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ንጉሴ አደሙ በበኩላቸው አዲስ ድርጅት ለመፍጠር ያስፈለገው ባሉት ድርጅቶች ውስጥ ገብቶ ለመታገል ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱና እርስ በርስ መጓተቱ በመበርከቱ ነው ሲሉ ለተሰብሳቢው ገልጸዋል።

ጠላታችን ሕወሃት ብቻ ነው።ሙሉ ጊዜያችንና ጉልበታችንን የአማራው ህልውና ጠላት በሆነው ሕወሃት ላይ እናተኩራለን ከሌሎች የለውጥ ሃይሎች ጋርም ተባብረን እንሰራለን ብለዋል።