የአብዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ተቃውሞ ቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 28/2011) የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ተቃውሞ ቀሰቀሰ።

ትላንት በክብር ተሸኝተዋል የተባሉት የቀድሞ የፓርቲው አመራሮች በፈጠሩት ጫና የለውጥ ሃይል በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እንዳይገባ ከጥቆማ አንስቶ ጫና በመፍጠር ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በማዕከላዊ ኮሚቴው ምርጫ አብዛኞቹ የአቶ ስዩም አወል አመራር ደጋፊዎች በዕጩነት መቅረባቸው ታውቋል።

የአፋር ወጣቶች ከወዲሁ የማዕከላዊ ኮሚቴውን ምርጫ በመቃወም ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የተቃውሞ ሰልፎች በተለያዩ የአፋር ከተሞች ሊደረግ ጥሪ ቀርቧል።

ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለው የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አብዴፓ ጉባዔ በአምስተኛ ቀኑ ተቃውሞን አስተናግዷል።

ተቃውሞው በጉባዔው አዳራሽ ሳይወሰን በመላ የአፋር የለውጥ ደጋፊ ህብረተሰብ ዘንድ መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ለተቃውሞ ሰልፍ እንዲዘጋጁ እያደረገ ነው።

ከፌደራል መንግስቱና ከአፋር ህዝብ ከፍተኛ የሆነ ግፊት የተደረገባቸውና ስልጣናቸውን እንዲያስረክቡ የተጠየቁት አቶ ስዩም አወል ለሁለት ሳምንት የተዘጋጁበትንና ከደጋፊዎቻቸው ጋር የመከሩበትን ውሳኔ በዛሬው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ላይ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው።

ስልጣኔን አለቅም፣ ከለቀኩም እኔ ለመረጥኩት ሰው አስረክባለሁ በሚለው አቋማቸው ወራትን የገፉት የፓርቲው ሊቀመንበርና የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ስዩም አወል በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ አቋማቸውን ቀይረው እንደነበረ ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።

አቶ ስዩም ከአዲስ አበባ መልስ ሰመራ እንደደረሱ ከየወረዳውና ቀበሌው የእሳቸው ጎሳ አባላትንና ደጋፊዎቻቸውን በመሰብሰብ ስራ ላይ ተጥምደው ቆየተዋል።

በዋናነት ዘመዳቸው የእሳቸውን ቦታ እንዲተካ በጽኑ ሲታገሉ የከረሙት አቶ ስዩም የጎሳ ግጭት በመቀስቀስ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም እንደተዘጋጁ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ከስምምነት ከደረሱባቸው ጉዳዮች ዋና አመራሩ ላይ ለውጥ ይደረግ፣ አዲስና ወጣት ትውልድ ወደፊት እንዲመጣ ይደረግ የሚል እንደነበረ የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች አቶ ስዩም ከስምምነቱ ውጪ የእሳቸው ደጋፊዎች የማዕከላዊ ኮሚቴውን እንዲቆጣጠሩ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

አምስተኛ ቀኑን በያዘው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጉባዔ ላይ እሳቸውን ጨምሮ 72 ነባር አመራሮችን ያሰናበተ ቢሆንም ዛሬ በተጀመረው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ሆን ተብሎ የአቶ ስዩም ደጋፊዎች እንዲመረጡ መደረጉ ተቃውሞን አስነስቷል።

አቶ ስዩም በእጅ አዙር ፓርቲውንና ክልሉን ለመቆጣጠር በማቀድ በምርጫው ላይ ጫና ፈጥረው የእሳቸው ደጋፊዎች እንዲቆጣጠሩት አድርገዋል ተብሏል።

የአፋር ህዝብን ያማረሩና ተቃውሞ ሲቀርብባቸው የነበሩ ግለሰቦች በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ በብዛት መመረጣቸውን የገለጹት የኢሳት ምንጮች ጉዳዩ ከፍተኛ ተቃውሞ ሊያስነሳ እንደሚችል ከወዲሁ እየተነገረ ነው ብለዋል።

ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ጥቆማ እንዲሰጥ ከማድረግ አሰራር ጀምሮ አድሏዊነት በታየበት  በትላንቱ ስብሰባ ጥቆማውን የተሰናበቱ አመራሮች እንዲሰጡ በማድረግ የለውጥ ሃይሎች ወደ አመራርነት እንዳይመጡ ተደርገዋል ተብሏል።

የአፋር ወጣቶች በሚቀጥሉት ቀናት በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ ለማደረግ ጥሪ እያስተላለፉ መሆኑንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።