የአሜሪካ ፌደራል መንግስት ተቋማት በከፊል ተዘጉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 25/2011)በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና በኮንግረሱ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የአሜሪካ ፌደራል መንግስት ተቋማት በከፊል ከተዘጉ 10 ቀናት አለፈ።

ችግሩን በንግግር ለመፍታት ትላንት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር የተደረገውም ውይይት ያለውጤት አብቅቷል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር ላይ ለመገንባት ላቀዱት ግንብ የጠየቁት 5 ቢሊዮን ዶላር በምክር ቤት ተቀባይነት አለማግኘቱ የፈጠረው ውዝግብ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ከስራ ውጭ አድርጎ ሁለተኛውን ሳምንት አስቆጥሯል።

ምክር ቤቱ በበጀቱ ላይ ባለመስማማት አላጸድቅም ሲል ወይንም ፕሬዝዳንቱ አልፈርምም በማለቱ ሳቢያ የሚከተለው የመንግስታዊ ስራ መስተጓጎል በቀደሙት የአሜሪካ መሪዎችም የታየ፣ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የስልጣን ዘመንም ለሶስተኛ ጊዜ የተመዘገበ ሆኖ ተገኝቷል።

በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን ከኦባማ ኬር የጤና ሽፋን ጋር በተያያዘ ምክር ቤቱ በጀት አላጸድቅም በማለቱ 13 ቀናት የፌደራል መንግስቱ ስራ በመስተጓጎሉ 2.1 ሚሊዮን ከሚሆኑ የፌደራሉ መንግስት ሰራተኞች 800 ሺህ ያህሉ ከስራ ውጭ ሆነው መቆየታቸውም በወቅቱ ተመዝግቧል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከታህሳስ 22 ጀምሮ ለተከሰተው ሁኔታ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ትላንት በኋይት ሃውስ የተወያዩት ኮንግረሱና የሴኔቱ መሪዎች አንዳችም የተጨበጠ ነገር ላይ ሳይደርሱ መለያየታቸውን ገልጸዋል።

የኮንግረሱና የሴኔቱ የዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪዎች ከኋይት ሃውስ እንደወጡ በሰጡት መግለጫ የድንበር ቁጥጥር መጠናከር እንዳለበት እነርሱም እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

የመንግስት በጀት በዚህ ሳቢያ መታገት እንደሌለበት ለፕሬዝዳንቱ መናገራቸውንም አስረድተዋል።

በተለይም በሴኔቱ የአነስተኛው ድምጽ ዲሞክራት ፓርቲ መሪ የሆኑት ሚስተር ቸክሹመር በሰጡት መግለጫ “ፕሬዝዳንት ትራምፕን በጀቱ ሳይጸድቅ የመንግስት ተቋማት ተዘግተው ስለሚቀጥሉበት ሁኔታ አንድ ተጨባጭ ምክንያት ይሰጠኝ ብዬ ጠይቄያቸዋለሁ፣ ሆኖም የሚያጠግብ ምላሽ አላገኘሁም” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ከውውቱ በኋላ በቲውተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “የዚህ ሃገር ሕዝብ እኔ ትክክለኛ መሆኔን የሚያምን ይመስለኛል”ብለዋል።

የበጀቱ መለቀቅና የፌደራል መንግስት ተቋማት መከፈት ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ያሳሰቡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሜክሲኮና አሜሪካ ድንበር ላይ እገነባዋለሁ ላሉት ግንብ የ5 ቢሊየን ዶላር በጀት ጥያቄያቸውን ገፍተውበታል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሚስተር ማይክ ፔንስ ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድመው ከዲሞክራቱ የሴኔት መሪ ቻክ ሹመር ጋር በመነጋገር ያቀረቡትን የ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በጀት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አልቀበልም ማለታቸው ይታወሳል።

ትላንት ረቡዕ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ያደረጉት ንግግር ምንም ውጤት አላመጣም ያሉት የዲሞክራት ፓርቲ መሪዎች ነገ አርብ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ለመነጋገር በድጋሚ መቃጠራቸውንም አስታውቀዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከታህሳስ 22/2018 ጀምሮ የፌደራል መንግስት ተቋማትን በከፊል ለመዝጋት ምክንያት የሆነው ውዝግብ መቋጫ ሳያገኝ ሁለተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል።

በዚህም በርካታ የመንግስት ተቋማት የቱሪዝም ማዕከላትን ጨምሮ መረጃ የሚሰጡ የአሜሪካ መንግስት ድረገጾችም ስራቸውን አቁመዋል።