የአሜሪካ የኢሚግሬሽንና ጉምሩክ ባለስልጣን ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታወቀ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 14/2010) የስራ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሆቴሎችና በልዩ ልዩ ቦታዎች አገልግሎት በሚሰጡ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ የአሜሪካ የኢሚግሬሽንና ጉምሩክ ባለስልጣን ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

በዋናነት በአሰሪዎቹ ላይ ያነጣጠረውና ተቀጣሪዎቹንም የማይተወው ርምጃ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ክስ መመስረትንም ይጨምራል።

ተቀጣሪዎቹ ደግሞ በሌላ ወንጀል የሚፈለጉ ካልሆነ በቀር ከአሜሪካ እንዲባረሩ ይደረጋል ብሏል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ።

በግዙፎቹ የንግድ ተቋማት ላይ የተነጣጠረ ነው የተባለው የአሜሪካ የኢሚግሬሽንና ጉምሩክ ባለስልጣን ርምጃ በዋናነት በአሰሪዎቹ ላይ ትኩረት ቢያደርግም ተቀጣሪዎቹንም እንደማይተው አስታውቋል።

ሕገወጦችን በማስተናገድና የሰዎችን ጉልበት አላግባብ በመበዝበዝ በሚል በአሰሪዎች ላይ ክስ እንደሚመሰርት ሲያስታውቅ ተቀጣሪዎቹ ደግሞ በሌላ ወንጀል የሚፈለጉ ካልሆነ ከአሜሪካ እንዲባረሩ ይደረጋል ሲል ያክላል።

በሆቴልና በአጠቃላይ ከምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ተቀጥረው ከሚሰሩ ሰራተኞች 9 በመቶ ያህሉ ህገ ወጥ ወይንም የስራ ፈቃድ የሌላቸው መሆናቸውንም ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል።

ርምጃው በቀጣዮቹ ሳምንታት እንደሚጀመርም ታውቋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 27/2015 ፋራክ ቤይግ የተባለ የሰቨን ኢለቨን ሱቅ ባለቤት ሕገወጥ ስደተኞችን በማሰራት በፈጸመው ሕገ ወጥ ድርጊትና የሰራተኞቹን ጉልበት በመበዝበዝ ተጠያቂ መሆኑን ሪፖርቱ ያስታውሳል።

147 ያህል የሰቨን ኢለቨን ሱቆች ያለው ፋራክ ቤይግ ከ13 አመታት በላይ ከአንድ መቶ በላይ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ቀጥሮ በመንግስት ከተቀመጠው ዝቅተኛ ክፍያ በታች እየከፈለ የሰራተኞቹን ጉልበት ጭምር በመበዝበዝ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንዳስቀረባቸውም ተመልክቷል።

ይህ በየቦታው የቀጠለ ድርጊት በመሆኑ ተመሳሳይ ርምጃ ለመውሰድ የኢሚግሬሽንና ጉምሩክ ባለስልጣን መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የኢሚግሬሽንና ጉምሩክ ተቆጣጣር ተቋም ተጠባባቂ ዳይሬክተር ቶም ሆማን እንደተናገሩት ርምጃው በአሰሪዎችም ሆነ በተቀጣሪዎቹ ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም ከሕግ አስከባሪዎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ የሆኑ ተቀጣሪዎች የመስሪያ ቪዛ ሊሰጣቸው እንደሚችልም ይፋ ሆኗል።

በሕገ ወጥ መንገድ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ድርጊቱን ራሳቸው ካጋለጡና በአሰሪዎቻቸውም ላይ ለመመስከር ከተዘጋጁ በአሜሪካ ጊዜያዊ መኖሪያ /ዩ ቪዛ/እንደሚሰጣቸውም ተመልክቷል።