የአማራ ክልል ምክር ቤት የህግ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በንፁሐን ዜጎች ላይ የተፈጠረውን እንግልት ፣ ማሰቃየት እና እስር አወገዘ፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት የህግ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በንፁሐን ዜጎች ላይ የተፈጠረውን እንግልት ፣ ማሰቃየት እና እስር አወገዘ፡፡
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 5 ቀን 2010 ዓ/ም ) ዛሬም ድረስ በክልሉ ተመሳሳይ ድርጊት እየተፈፀመ መሆኑንም- ባካሄደው የመስክ ምልከታ ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡
የምክር ቤቱ የህግ ጉዳዩች አሰተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ የሆኑት አቶ አማረ ሰጤ በአሁኑ ስዓት እየተካሄደ በሚገኝው የአማራ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር ፣ 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን ፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉን ፍትህ ቢሮ እና የአሰተዳደደር ፀጥታ ጉዳዩች ቢሮ የ2010 ዓ.ም የቅርብ ጊዜ ምልክታዎችን እና የውሳኔ ሃሳብ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ፣በፌድራል ማረሚያ ቤት የተፈጠረው ግፍ በክልሉ ባሉ ማረሚያ ቤቶችም እየተደገመ ነው ብለዋል፡፡
በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች አሁንም ክስ ሳይመሰረትባቸው እንደሚንገላቱ፣ በአሰቸኳይ አዋጁ የተያዙ የኮማንድ ፖስቱ እስረኞች የት እንደገቡ እንደማይታወቁ ፣ ከአንድ ቤተሰብ እስከ አራት የሚደርሱ ሰዎች ታፍነው እንደጠፉ ፣ ያለ ፍትህ ከስድስት ወራት እስከ አመታት የታሰሩ ወገኖች እንዳሉ አቶ አማረ አመልክተዋል።
እንደ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገለጻ፣ ቋሚ ኮሚቴው ቁጥጥር ባደረገባቸው የሞጣ ፣የንፋስ መውጫ ፣ የደባርቅ እና የፍኖተሰላም ማረሚያ ቤቶች እስከ ስድስት ወራት ያለ ክስ የታሰሩ ወገኖች ተገኝተዋል፡፡
በህግ ተጠርጣሪዎች ላይ አስከፊ ድብደባ በመፈፀም ላበይ ጋይንት ወረዳ ፖሊስ፣ እንዲሁም
ተጠርጣሪ ከተያዘ በኃላ የፈላ ውሃ በመድፋት በባህር ዳር ከተማ ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ፣ በ1ኛ ፖሊስ ጣቢያ ፣ በዳንግላ ፣ ላበይ ጋይንት ፣ በባህር ዳር 1ኛ እና በፖሊስ ጣቢያዎች ከፍተኛ ግፍ እንደሚፈፀም የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን ኢሰበዓዊ ድርጊት በፈፀሙ አካላት ላይ እርምጃ አለመውሰዱን የኢትዮጵያ ሰበዓዊ መብት የባህር ዳር ቅርንጫፍ አረጋግጧል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ባለፈው ሁለት ሳምንት በሞጣ ፣በንፋስ መውጫ ማረሚያ ቤት ፣ በደባርቅ እና በፍኖተሰላም ማረሚያ ቤቶች ባደረገው የመስክ ምልከታም ይህንኑ እውነታ በእስር ቤቶቹ ከሚገኙ ታራሚዎች አረጋግጧል፡፡
በሁሉም ማረሚያ ቤቶች የሚታዩ ታራሚዎችን በማረሚያ ቤት ውስጥ በካቴና በማሰር ፣ ለይቶ በማሰር እና በዛቻና ማስፈራሪያ ማሸማቀቅ በወልድያ ፣ በደብረታቦር እና በአዲስ ዘመን ማረሚያ ቤቶች ጎልቶ ታይቷል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምንም ዓይነት ችግር የሚፈታ የፍትህ ስርዓት አለመዘርጋቱ ተመልክቷል።
” ዜጎች በፍትህ እጦት እና ተደራሽነት እየተሰቃዩ ነው፡፡ አቃብያነ ህጎችም ፍትህን በመሸጥ እና በመለወጥ ፣ ታጥረዋል፡፡ የፍትህ ንግድ በጠበቆች እና በዓቃብያነ ህጎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ የድሃ እንባ ግን አሁንም አልታበሰም” ብለዋል፡ ሰብሳቢው አቶ አማረ።