የአማራና ኦሮምያ ክለብ ደጋፊዎች ህውሃትን ኣወገዙ

(ኢሳት ዜና – ሃምሌ 3 , 2009 )  

የኦሮምያና የአማራ እግር ኳስ ክለቦች ደጋፊዎች በባህርዳር ስታዲየም የጋራ ትብብር ባማሳየት የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ ህውሃት / አገዛዝን አወገዙ ።

የባህርዳር ከተማ ክለብና የኦሮምያ ለገጣፎ እንዲሁም የአማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት / አውስኮድ / ከሱሉልታ ጋር ሲጫወቱ የየክለቦቹ ደጋፊዎች በወዳጅነት መንፈስ በጋራ ሲጨፍሩ ታይተዋል::

በውድድሩ በባህርዳር ከተማና ለገጣፎ ተጫውተው 0 ለ 0 ሲለያዩ ሱሉልታ አውስኮድ ቡድን 1 ለባዶ አሸንፏል ።

በዚሁም ጊዜ በባህርዳር አጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎች  የአማራና የኦሮምያ ደጋፊዎች በትብብር ስሜት ሆነው የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ / ህውሃትን /አገዛዝ አውግዘዋል ።

ደጋፊዎቹ የክለባቸውን አርማና ኮከብ የሌለበት የኢትዮጵያ ባንዲራ ይዘው የኦሮሞና የአማራ ህዝብ አንድ መሆኑን የሚያሳዩ ዜማዎችን ሲያሰሙ ውለዋል ።

የአማራና የኦሮምያ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ህብረታቸውን በወዳጅነት ስሜት በጭፈራ ሲያሳዩና ህውሃትን ሲያወግዙ በፌዴራል ፖሊሶች ከመከበባቸው ውጪ የደረሰባቸው ጉዳት የለም ።

በአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት ጊዜ የኦሮሞ ደም ፥ ደሜ ነው በማለት በጎንደርና በባህርዳር ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች ህብረታቸውንና አጋርነታቸውን ማሳየታቸው ይታወሳል ።