የአማራተ ወላጆች ከቡሎ ዴዴሳ ቀበሌ እንዲወጡ የታዘዙበት ደብዳቤ ከተጻፈ ጀምሮ ሁሉም የአማራተወላጆች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ተፈናቃዮች ገለጹ

የአማራተ ወላጆች ከቡሎ ዴዴሳ ቀበሌ እንዲወጡ የታዘዙበት ደብዳቤ ከተጻፈ ጀምሮ ሁሉም የአማራተወላጆች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ተፈናቃዮች ገለጹ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 02 ቀን 2010 ዓ/ም) ንጉሴ ጀርሞሳ በተባለው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቦሎዴዴሳ ሊ/መንበር የተጻፈው ደብዳቤ “የአማራ ተወላጆች በሙሉ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2010ዓም ወይም እስከ ሚያዚያ 10/2010 ዓም ሃብታቸውንና ንብረታቸውን ሽጠው ወይም አርደው እንዲወጡ” ያዛል። ይህንን ትዕዛዝ አክብረው የማይወጡ የአማራ ተወላጆች “በህግ ተገደው እየታሰሩ እንደሚወጡ ለሚደርሰው ጉዳትም የቀበሌው መስተዳደር ተጠያቂ እንደማይሆን” ሊቀመንበሩ አቶ ንጉሴ ጀርሞሳ ገልጸዋል ።
ጉዳዩን በማስመልከት ደብዳቤውን ካገኙት ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ስለ ሁኔታው ሲገልጹ፣ ደብዳቤው ለአንድ ቀን ተለጥፎ እንደነበርና ግለሰቡ ባሰማራቸው ሰዎች አማካኝነት ትእዛዝ ሲሰጥ እንደነበር ለኢሳት ገልጸዋል። የቀበሌው ሊቀ መንበር ብቻውን ደብዳቤውን ጽፎታልብለው እንደማያምኑ የሚገልጹት አባወራው፣ የወረዳው እና የክልሉ ባለስልጣናት ሳያውቁት አቶ ንጉሴ በራሱ ደብዳቤውን ሊጽፈው አይችልም ብለዋል ።
አቶ ንጉሴ ከተቃዋሚነት ወደ ኢህአዴግን አባልነት ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ ከወረዳ ባለስልጣናት ጋር ሆኖ በአማራ ተወላጆች ላይ ስቃይ ሲፈጽም እንደነበርም አክለው ገልጸዋል ። በቦሎዴዴሳ በእርሻና በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ 3 ሺ የሚጠጉ የአማራ ተወላጆች በተለያ የጊዜ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ተፈናቃዮች ተናግረዋል።
በባህርዳር ከተማ በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዮች ወደመጡበት ክልል እንዲመለሱ የብአዴን ባለስልጣናት ተፈናቃዮችን ለማግባባት ቢሞክሩም፣ ተፈናቃዮቹግን ከዚህ በፊት የተደረገው ተደጋጋገሚ ሙከራ ውጤት አለማምጣቱን በመጥቀስ ተመልሰው ለመሄድ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ ለባለስልጣናቱ ገልጸውላቸዋል ።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ የአማራ ተወላጆች በተደጋጋሚ ቢፈናቀሉም እስካሁን ተጠያቂ የሆነ ባለስልጣን የለም።