የንጉስ አጼ ሃይለስላሴ ሐውልት በመጠናቀቅ ላይ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 16/2011) በአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት ውስጥ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉስ አጼ ሃይለስላሴ ሐውልት ስራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ለአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ከፍተኛ ሚና ተጫውተው ሳለ አስተዋጽኧቸው ግን መዘንጋቱና የክዋሜ ንክሩማህ ሐውልት ብቻ መቆሙ ብዙዎችን ያነጋገረ ነበር።

በአፍሪካ ሕብረት ምስረታም ሆነ የአፍሪካ ሃገራት ከቅኝ ግዛት ለመውጣት በሚያደርጉት ትግል በኢትዮጵያ መሪነታቸው ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ንጉስ ሃይለስላሴ ሐውልታቸው በአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት ውስጥ እንዲቆም ከፍተኛ ተጽእኖ ያደረጉት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና መንግስታቸው እንደነበርም ሲገለጽ ቆይቷል።

የዛሬው የአፍሪካ ሕብረት ከ55 አመት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 25/1963 የአፍሪካ አንድነት ሆኖ በአዲስ አበባ በ32 የአፍሪካ ሃገራት ሲመሰረት የአስተናጋጇ ሃገር ርዕሰ ብሔርና የመጀመሪያውን የድርጅቱን ጸሐፊ አቶ ክፍሌ ወዳጆን የሰጡት ንጉስ ሃይለስላሴ የአፍሪካ ሃገራት የካዛብላንካና ሞኖሮቪያ በሚል በሁለት ቡድን ሲከፈሉ ወደ አንድ እንዲሰበሰቡና በጋራ እንዲቆሙ አብይ ሚና መጫወታቸውም ሲገለጽ ቆይቷል።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንደ አውሮፓውያኑ በ2002 ወደ አፍሪካ ሕብረትነት መሸጋገሩን ተከትሎ በቻይና መንግስት ሙሉ ወጪ አዲስ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ መከፈቱም ይታወቃል።

በቻይና መንግስት ሙሉ ድጋፍ በ200 ሚሊየን ዶላር ወደ አንድ መቶ ሜትር ርዝመት ያለው ግዙፍና ዘመናዊ ህንጻ ከ6 አመት በፊት ሲጠናቀቅ የመታሰቢያ ሐውልት የቆመው ለቀድሞው የጋና መሪ ዶክተር ክዋሜ ንክሩማህ ብቻ ነበር።

ይህ ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰ ቢሆንም የአፍሪካ ሕብረት በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ ስላልቀረበበት ሳይቀበለው ቆይቷል።

አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ ጉዳዩ እንደገና የተንቀሳቀሰ ሲሆን በዚህም ተቀባይነት በማግኘቱ የአጼ ሃይለስላሴ ሐውልት ግንባታ ተጀምሯል።

ከሁለት ወር በኋላ በፈረንጆቹ አዲስ አመት መጀመሪያ በጥር ወር 2011 ሐውልቱ እንደሚመረቅም ከወጣው መርሐ ግብር መረዳት ተችሏል።