የነዳጅ አቅርቦትን ለማስተጓጎል የታቀደው ዘመቻ ነገ ይጀመራል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 3/2010) በቄሮ የተጠራውና የነዳጅ አቅርቦትን ለማስተጓጎል የታቀደው ዘመቻ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ለአንድ ሳምንት በሚካሄደው በዚሁ ዘመቻ ቦቴዎች ከውጭ ሃገር ነዳጅ ጭነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ይደረጋል።

በሃገር ውስጥም ነዳጅ ጭነው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሏል።

ዘመቻው የሚጀመረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በርካታ ሰዎች በመገደላቸው ነው።

በቄሮ የተጠራው የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው።

የአገዛዙን ገዳይና ጨቋኝ አካሄድ ለመግታት በዚሁ ዘመቻ ከውጭ ሃገር የሚገቡም ሆነ በሐገር ውስጥ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ የነዳጅ መጫኛ ተሽከርካሪዎች የጥቃት ኢላማ ይሆናሉ ተብሏል።

የኦሮሚያ ቄሮዎች ያወጡት መግለጫ እንደሚያመለክተው ይህን ዘመቻ እያወቁ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ለሚደርስባቸው ጥቃት ሃላፊነቱን ራሳቸው ይወስዳሉ።

እናም በተሽከርካሪዎቹ ላይ ርምጃ ከመወሰዱ በፊት ማዕቀቡን አክብረው እንዳይንቀሳቀሱ ቄሮዎች እንመክራለን ብለዋል።

በቄሮዎቹ መግለጫ መሰረት የነዳጅ አቅርቦትን ለማስተጓጎል የሚካሄደው ዘመቻ በጥንቃቄ የሚካሄድ መሆኑም ታውቋል።

የሚወሰደው ርምጃ በከተሞች ውስጥ ያሉ የነዳጅ ማደያዎችን አይመለከትም።

ይህም ጥንቃቄ የሚደረገው በሚወሰደው ርምጃ ሰላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ ለማድረግ ነው ተብሏል።

የኦሮሚያ ቄሮዎች ከአድማና ሰላማዊ ሰልፍ ወደ ሌላ ተቃውሞ ስትራቴጂ በመሸጋገር የነዳጅ አቅርቦትን ለማስተጓጎል እርምጃ ለመግባት የተገደዱት በአስቸኳይ አዋጁ ሰበብ የዜጎችን ሕይወት ያለርህራሄ እየተቀጠፈ በመሆኑ ነው ብለዋል በመግለጫቸው።

ሕዝቡ የቄሮዎችን ትግል እንዳይደግፍና የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎችም ጥቃት እንደሚፈጸም አውቀው ከመንቀሳቀስ እንዲታቀቡ መግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሞያሌ በንጹሃን ዜጎች ላይ በከፈቱት ተኩስ 13 ዜጎችን ገድለው ከ15 በላይ ማቁሰላቸው ይታወሳል።

ግድያውንም በስህተት የተፈጸመ ሲሉ ሽፋን ለመስጠት እየሞከሩ መሆናቸው ይታወቃል።

ይሕ በአንዲህ እንዳለም የቄሮዎችን የነዳጅ ዕቀባ ጥሪ ተከትሎ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ነዳጅ ማደያዎች በወረፋ መጨናነቃቸውን በፎቶግራፍ ተደግፈው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።