የትግራይ ልዩ ሃይል ከወልቃይትና ራያ እንዲወጣ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 16/2011) የትግራይ ልዩ ሃይል ከወልቃይትና ራያ ወጥቶ በምትኩ የፌደራል ፖሊስ እንዲገባ ተጠየቀ።

ልሳነ ግፉአን የተሰኘው የወልቃይት ጠለምት ጠገዴ መብት ተሟጋች ድርጅት በራያ እየተካሄደ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ወገንተኛ የሆነው የትግራይ ልዩ ሃይል ሰላም የሚያስከብር ባለመሆኑ ገለልተኛ የሆነ አካል በአካባቢው መስፈር ይገባዋል።

ከራያ ተወላጆች ጎን እንቆማለን ያለው ልሳነ ግፉአን ህወሃት በቀረጸው ህገመንግስትም ሆነ በህወሃት በተዋቀረው ፌደራል ስርዓቱ የማንነት ጥያቄዎች ፈጽሞ ሊመለሱ አይችሉም።

በሌላ በኩል በራያ ተወላጆች ላይ የትግራይ ልዩ ሃይል የሚወስደውን አፈና ግድያና እስር በመቃወም በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ሰልፍ ተጠርቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በአላማጣ አፈሳውና እስሩ ለስድስተኛ ቀን መቀጠሉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ህወሃቶች የማንነት ጥያቄ ህገመንግስቱን የሚያፈርስ ነው የሚል አቋም እያንጸባረቁ በሚገኙበት በዚህን ወቅት ከየአቅጣጫው ለራያዎች ድጋፍ እየተሰጠ ነው።

በወልቃይት ጠለምትና ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ላይ ድጋፍ በማድረግ የሚንቀሳቀሰው ልሳነ ግፉአን የራያን ህዝብ መሬት ለመዝረፍና ማንነቱን በሃይል ለመጨፍለቅ የሚደረገው አፈና ትግሉን ያጠናክረዋል እንጂ አያዳክመመው ሲል አጋርነቱን አሳይቷል።

ልሳነ ግፉአን ለኢሳት በላከው መግለጫ ላይ እንደገለጸው በወገናችን የራያ ህዝብ ላይ እንዲህ ዓይነት የጭካኔ ተግባር መፈጸሙ በእጁ አሳዝኖናል ብሏል።

በመሆኑም ሽብር ፈጣሪው የህወሀት ልዩ ሃይል በአስቸኳይ ከራያና ወልቃይት መሬት ለቆ እንዲወጣና በምትኩ የፌደራል ፖሊስ የአከባቢውን ሰላም እንዲያስከብር ለፌደራሉ መንግስት ጥሪ አቀርባለሁ ሲል ገልጿል ልሳነ ግፉአን።

በትግራይ ልዩ ሃይል ታፍነው የት እንደትወሰዱ የማይታወቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ የራያ ተወላጆች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የጠየቀው ልሳነ ግፉአን በጭካኔ ለተገደሉት ራያዎች ለቤተሰቦቻቸው ካሳ እንዲከፈልም ጠይቋል።

የራያና ወልቃይት የማንንት ጥያቄ በህውሀት እንደማይመለስ የገለጸው ልሳነ ግፉአን ጉዳዩን የህወሀት ህገመንግስት ሊፈታው የማይችለው ሲል ገልጿል።

ታሪካዊና ባህላዊ መሰረትን ባጠና መልኩ የማንነት ጥያቄን ለመመለስ የፌደራል መንግስቱ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል።

በሌላ በኩል በራያ ተወላጆች እየተፈጸመ ያለውን አፈና ግድያና እስር በማውገዝ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል።

የፊታችን እሁድ ጥቅምት 18 የጠራውን ሰልፍ የጠየቁ ከ10 በላይ ከተሞች ፍቃድ ማግኘታቸውን የደረሰን መረጃ ያመልክታል።

ባሕር ዳር፣ ወልዲያ፣ ጎንደር፣ ፍኖተ ሰላም፣ እንጅባራ፣ ደብረ ታቦር፣ደብረ ብርሃን፡ ደብረ ማርቆስ፣ ከሚሴ፣ ደሴና ሰቆጣ ዕሁድ ዕለት ለራያዎች አጋርነታቸውን ለማሳየት አደባባይ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከራያ በተጨማሪ አደጋ ላይ የወደቀውን ጣና ሀይቅንና በላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ላይ የተጋረጠውን የመፍረስ አዝማሚያ በማንሳት ትኩረት እንዲሰጠው የሚጠይቅ ይሆናልም ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በአላማጣ ዛሬም አፈናና እስር በመካሄድ ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ስድስተኛው ቀኑን በያዘው የትግራይ ልዩ ሃይል ርምጃ በርካታ የራያ ተወላጆች እየታሰሩ መሆኑ ታውቋል።

አንድ ሳምንት ባስቆጠረው የአላማጣ ውጥረት የታሰሩት ሰዎች ቁጥር በትትክል ባይታወቅም ከ500 በላይ እንደሚሆን ግምቶች አሉ።

አምስት ሰዎች በትግራይ ልዩ ሃይል በተሰውደ ርምጃ መገደላቸው የሚታወስ ነው።