የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 9/2010) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 2 ነጥብ 8 ሚሊየን መደረሱ ተገለጸ።

ከስድስት ወራት በፊት ከነበረው በአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊየን መጨመሩንም የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ተቋም ዩኒሴፍ አስታውቋል።

መፈናቀሉ የተከሰተው በአብዛኛው በኦሮሚያ፣ ሶማሌና ደቡብ ክልሎች መሆኑንም ዩኒሴፍ ባወጣው መረጃ ተገልጿል።

ከክረምቱ መጠናከር ጋር ተያይዞ በሚከሰት የጎርፍ አደጋ ተጨማሪ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ በመግለጽ ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል ብሏል ዩኒሴፍ።

የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ተቋም ዩኒሴፍ እንዳስታወቀው በ6ወራት ውስጥ ብቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ የመፈናቀል ሰለባ ሆኗል።

ከጥር ወር በፊት አንድ ነጥብ 2 ሚልዮን የነበረው የተፈናቃይ ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ሁለት ነጥብ ስምንት መድረሱን ነው ዩኒሴፍ በሪፖርቱ ያመለከተው።

መፈናቀሉ በስፋት ከተከሰተባቸው አከባቢዎች በዩኒሴፍ ሪፖርት የተጠቀሱት ሶስት ክልሎች ናቸው – ኦሮሚያ፡ ሶማሌና ደቡብ ክልሎች።

በእነዚህ ሶስት ክልሎች የተከሰተው መፈናቀል መንስዔአቸው የእርስ በእርስ ግጭቶችና ተፈጥሮአዊ አደጋ መሆኑ ተገልጿል።

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች መሀል በተፈጠረ ግጭት ከ1ሚሊየን በላይ ሰዎች ከሁሉቱም ወገኖች መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።

በጉጂና ጌዲኦ ብሄረሰቦች መሀል የተፈጠረው ግጭትም ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ እንዲኖር ማድረጉም ይታወቃል።

ዩኒሴፍ በሪፖርቱ እንዳመለከተው እነዚህን ተፈናቃዮች ለመርዳት ከ100ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል።

እስከአሁን የተገኘው ከ31በመቶ እንደማይበልጥ ነው ዩኒሴፍ ያስታወቀው።

ኢትዮጵያ እያሻቀበ ከመጣው የሀገር ውስጥ መፈናቀል በተጨማሪ ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጋ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞችን ማስጠጋቷ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከሶማሊያ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የተስደዱ 920ሺህ ሰዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የመጠለያ ካምፖች እንደሚገኙ ዩኒሴፍ በሪፖርቱ አመልክቷል።

ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ማሻቀብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሰቦኣዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ።

ተፈናቃዮቹን መልሶ ለማቋቋም በኢትዮጵያ አቅም የሚቻል ባለመሆኑ ዓለም ዓቀፍ ትብብር ተጠይቋል።

ዩኒሴፍ በሪፖርቱ መጪውን ጊዜ ከስጋት ጋር እንደሚጠብቀው ገልጿል።

በተለይም ከክረትም መጠናከር ጋር በተያያዘ 2ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ በጎርፍ አደጋ እንደሚጠቃ የገለጸው ዩኒሴፍ አሁን ካለው ተፈናቃይ በእጥፍ የሚጨምር ቁጥር ይመዘገባል የሚል ስጋት እንዳለውም አስታውቋል።

በዩኔሴፍ ሪፖርት የተጠቀሱት ተፈናቃዮች በሶስት ክልሎች የሚገኙ ሲሆን በሌሎች የኢትዮጵያ አከባቢዎች የተከሰቱት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተመሳሳይ መፈናቀሎች እንዳልተጠቀሱ ታውቋል።

በተለይ ከተለያዩ አከባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለዋል።

ከጅቡቲም ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።