የብአዴን አባልነትን ያልተቀበሉ ሠራተኛ “ከተማዋን ለቀህ ጥፋ” ተባሉ

መስከረም ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአማራ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ጐንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የአብርሃጅራ ከተማ ውስጥ የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባልነትን ያልተቀበሉ ሠራተኛ ከከተማዋ ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፤ የከተማወወ አስተዳደርና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት እየፈፀሙ ነው።

የአካባቢው ሹመኞችና የቢሮ ሀላፊዎች ራሳቸውን የተለዩ አድርገው ስለሚቆጥሩ የሠራተኞችንና የነዋሪዎችን  መብቶች በማናለብኝነት እየጣሱ ይገኛሉ ብለዋል-ነዋሪዎቹ።

የፍኖት ምንጮች አክለው እንደገለጹት፦  “ኃላፊዎች በማን አለብኝነትና በጀብደኝነት ሰዎችን በአመለካከታቸው

ብቻ እንደ ወንጀለኛ በመቁጠር ከህግ አግባብ ውጭ ከሥራ ያግዳሉ ያዋክባሉ፣ ያመናጭቃሉ ያንጓጥጣሉ።”

የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ሰለባ ሆነዋ ከተባሉት ሠራተኞች መካከል  አቶ አንጋው ተገኝ   “በእርግጥ ከፍተኛ በደልእየተፈፀመብኝ ነው፡፡ እኔ የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ሠራተኛ ነኝ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የብአዴን አባል እንድሆን ተጠየቅኩ፡፡ እኔ እንደ አንድ የመንግስት ሠራተኛ ሙያዊ ሥራ ከመሥራት ውጪ አባል መሆን እንደማልፈልግ ነገርኳቸው፡፡” ብለዋል።

ከዚያም፦”አንተ የተቃዋሚ ደጋፊ ስለሆንክ ቢሮ እንዳትመጣ! ከሠራተኛ ጋርም እንዳትገናኝ! ደሞዝህን ብቻ መጥተህ እንድትወስድ አሉኝ፡፡” ያሉት  አቶ አንጋው፤ “ እኔ ደሞዝ መውሰድ ያለብኝ ሥራ ሠርቼ  መሆን ስላለበት እባካችሁ ሥራዬን ልሥራ ብላቸው ከለከሉኝ >>ብለዋል።

ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው አንድ ዓመት ሙሉ ያለ ሥራ ደሞዝ እየተከፈላቸው መቆየታቸውን የጠቀሱት አቶ አንጋው፤ “ለረዥም ጊዜ ተከታትለውኝ ምንም ጥፋት ሊያገኙብኝ አልቻሉም። ይሁንና  ሰሞኑን ደግሞ፦” ሥራውንም፣!” ከተማውንም ለቀህ ሂድ የሚል ትዕዛዝ ደረሰኝ፡፡ የተወለድኩትም፣ ሥራዬም፣ ኑሮዬም እዚሁ ነው፡፡ የት ልሂድ? ብላቸው፤ ምንም የምናውቀው ነገር የለም! ወደ ፈለክበት ሂድ! >>ብለው ማስጠንቀቂያ ሰጥተውኛል>> ብለዋል።

“አቤት የምልበት ቦታ አላገኘሁም፡፡ የዜግነት መብቴም ተገፏል፡፡ እባካችሁ የሚሰማ የመንግስት አካል ካለ፤ ጩኽቴን አሰሙልኝ”ሲሉ አቶ አንጋው የተማጽኖ ጥሪ አቅርበዋል።

ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከታቸውን የጸጥታ ቦሮ ሀላፊውን አቶ ፋሲል ሰንደቁንና የቢሮው ሠራተኛ የሆኑትን አቶ ገብረመድህን ወንድምእሸትን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊሳካ አልቻለም።

የ አማራ ክልል የወጣቶች ማህበር ሀላፊ፤  ኢህአዴግ በዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ኢፍትሀዊ ድርጊት ማስቆም የሚቻለው በትጥቅ ትግል ብቻ ነው በሚል  ውሳኔ ሀላፊነቱን ለቅቆ ወደ ለአመፅ ትግል ወደ ጫካ እንደገባ መዘገባችን ያታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide