የብአዴን ነባር ታጋዮች በንቅናቄው 37ኛ ዓመት ክብረበዓል ላይ ሳይገኙ ቀሩ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 11/2010) የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብአዴን ነባር ታጋዮች በንቅናቄው 37ኛ ዓመት ክብረበዓል ላይ ሳይገኙ መቅረታቸው ተገለጸ።

በግብርና ስራ የተሰማሩና በኑሮ የተጎሳቆሉት የቀድሞ የንቅናቄው ታጋዮች ዛሬ የታወስንበት ምክንያት ሊገለጽልን ይገባል የማለት ተቃውሞ ማቅረባቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ብአዴን የተመሰረተበትን 37ኛ ዓመት ሲያከብር በመርሃግብር ከያዛቸው መርሃ ግብሮች አንዱ ለንቅናቄው ነባር ታጋዮች እውቅናና የምስክር ወረቀት መስጠት ነበር።

ይሁንንና የትም ወድቀው የቀሩና ብዙዎች በድህነት ተሰቃይተው የሞቱ መሆናቸውን የገለጹ አንዳንድ ነባር ታጋዮች ለዘመናት ተዘንግተን ዘንድሮ የምንታወስበትን ምክንያት ስላላወቅን በበዓሉ ላይ አንገኝም በማለት መቅረታቸው ታውቋል።

በተለይ በሰሜን ጎንደር በግብርና ስራ የተሰማሩ ነባር ታጋዮች አብዛኞቹ በዓሉን አንካፈልም በማለት ማደማቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ለኢሳት በደረሰው መረጃ መሰረት ነባር ታጋዮችን ለመሸለም በተያዘው መርሃግብር ምትክ የብአዴን የሊግና ፎረም አባላት የሆኑ ወጣቶች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

የአማራ ህዝብ በብአዴን እምነት እንደሌለውና ከአማራ ህዝብ ጥቅም ይልቅ ለህወሀት ስርዓት ህልውና ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ንቅናቄው ከህዝብ በሰበሰበው መጠይቅ ማረጋገጡን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በብአዴን ጽ/ቤት በተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት አብዛኛው የአማራ ህዝብ ብአዴንን የህወሀት ወኪል አድርጎ የመቀበል ዝንባሌ እንዳለው ታውቋል።

ብዙዎቹ የብአዴን አመራሮች ለስልጣን የበቁት በህወሀት መልካም ፍቃድ መሆኑን እንደሚረዱ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎች የአማራ ህዝብ በታሪኩ ከፍተኛ ውርደት የደረሰበት፣ በማንነቱ የተገደለበትና የተሰደደበት ዘመን የህወሀት መንግስት ስልጣን የያዘበት ዘመን እንደሆነ መግለጻቸውን የኢሳት ምንጮች ከላኩት መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብአዴን በሚያዘጋጃቸው ህዝባዊ መድረኮች ላይ ህዝቡ በግልጽ መናገር የጀመረ ሲሆን ‘’እናንተ የህወሀት ተላላኪዎች ናችሁ። በአማራ ስም የተፈናጠጣችሁ የህወሀት አሽከሮች ናችሁ’’ የሚል ተቃውሞ እየቀረበ ይገኛል።

በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ስር ሆኖ ዛሬ የተከበረው የብአዴን 37ኛ ዓመት ክብረበዓል ላይ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አለምነው መኮንን ለዚህ ነጻነት ያበቁን ታጋዮቻችን ምትክ የሌለውን ህይወታቸውን ሰውተውልናል ማለታቸው ተገልጿል።

አቶ አለምነው በአንድ ስልጠና ላይ የአማራውን ህዝብ በአስነዋሪ ቃላት በመሳደባቸው ከፍተኛ ተቃውሞ እንደቀረበባቸው የሚታወስ ነው።

በቅርቡ በተደረገ የተሃድሶ ግምገማ ከተባረሩት አብዛኛው የወረዳና የክልል አመራር ለህወሀት መልካም ስሜት የላችሁም በሚል ተገምግመው እንደሆነ የውስጥ ምንጮ ገልጸዋል።

የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ግምገማ ላይም ዋንኛው መመዘኛ አመራሩ ለህወሀት ያለው አመለካከት ሲሆን ከዚህ አንጻር መስመር ስተዋል የተባሉት ከሃላፊነታቸው ሊወገዱ እንደሚችሉም ይጠበቃል።

በ1969 ተጻፈው የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት ማኒፌስቶ የአማራውን ህዝብ ታሪካዊ ጠላት በሚል የፈረጀ ሲሆን እስካሁንም በድርጅቱ መተዳደሪያ ፕሮግራም ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።