የቂሊንጦ እስር ቤት አቃጥለዋል ተብለው ክስ የቀረበባቸው ታሳሪዎች የክስ ቻርጁን ወደ ዳኞችና አቃቢያነ ህጎች ወረወሩ

ኢሳት (ሰኔ 5 ፥ 2009)

ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በማቃጠል ጉዳት አድርሰዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች የታደላቸውን ክስ ቻርጅ ወደ ጃኞቹና አቃቢያነ ህጎቹ በመወርወር እንዲሁም በድምፅ ተቃውሟቸውን ማቅረባቸው ተገለጸ። ፍ/ቤቱም ሁኔታውን ተከትሎ የፍርድ ውሳኔ አሳልፏል።

የፍርድ ውሳኔው የተላለፈባቸው ተከሳሾች በቂሊንጦ እስር ቤት ደርሶ ከነበረው የእሳት ቃጠሎ አደጋ ጋር በተገናኘ ተደራራቢ ክስ ተመስርቶባቸው ከነበሩ 121 እስረኞች መካከል መሆናቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

ሰሞኑን ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት 21ዱ ተከሻሾች የተመሰረተባቸው ክስ ሊነበብላቸው ሲል “ክሱ አይነበብም” በማለት በችሎቱ ከፍተኛ ተቃውሞን አቅርበዋል። 

የተወሰኑ ተከሳሾች የተሰጣቸውን ክስ ግልባጭ ወደ አቃቤ ህግና ወደ ዳኞች የወረወሩ ሲሆን፣ “ዳኞችና አቃቤ ህጎች ጅቦች፣ ውሾች፣ ቆሻሾች፣ ሆዳሞች ናችሁ” የሚሉ ቃላትን መሰንዘራቸው ተመልክቷል።

እነዚሁ ከፍተኛ ተቃውሞን ያቀረቡት ተከሳሾች አቃቤ ህግን ለመደብደብ ሲሞክሩ ፖሊስ ጣልቃ በመግባት ሁኔታውን ማረጋጋቱንም ለመረዳት ተችሏል።

ሌሎች ጸያፍ ድርጊቶችን ጭምር ፈጽመዋል የተባሉት ተከሳሾች ፍርድ ቤቱን እንዲሁም በስራ ላይ ያለን ዳኛ የተዳፈረ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የአንድ አመት ፅኑ እስራት እንደተላለፈባቸው በሪፖርቱ ሰፍሯል።

በእያንዳንዳቸው ተከሳሾች ላይ የተላለፈው የአንድ አመት ፅኑ እስራት እስኪጠናቀቅ ድረስ በተከሳሾች ላይ ሲካሄድ የነበረው የክስ ሂደት እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን በአብላጫ ድምፅ ቢያጸድቅም አንድ ዳኛ በፍርዱ በሃሳብ መለየታቸውን ጋዜጣው በዘገባው አመልክቷል። የተለየ ሃሳብን ያቀረቡት ዳኛው ተከሳሾች “ተበድለናል አዳምጡን፣ ጉዳት ደርሶብናል፣ በዚሁ ሁኔታ ክስ የመስማት አቅም የለንም” ሲሉ ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢ መልስ ማግኘት እንደነበረበት በችሎት ልዩነታቸውን አሰምተዋል።

ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ ተገቢ ጊዜ የሚፈልግና ምናልባትም ላቀረቡት አቤቱታ ተገቢ መልስ ሊያገኙ ቢችሉ አለመግባባቱ ሊተው ይችል እንደነበር ዳኛው አክለው አስረድተዋል።

እንዲሁም የትኛው ተከሳሽ እንደተናገረ ባልጠረጋገጠበት ጉዳይ ዝም ብለው የተቀመጡትን ተከሳሾች የሚጎዳ ቅጣት መወሰኑ ተገቢ እንዳልሆነ ዳኛው አስታውቀዋል።

ከቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ጋር በተገናኘ ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙት ተከሳሾች ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ ለረጅም ሰዓት እጃቸው በሰንሰለት ይታሰርና በጨለማ ክፍል እንዲቆዩ መደረጉን ለችሎት ባሰሙት አቤቱታ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።

እነዚሁ ተከሳሾች ተመሳሳይ አቤቱታን በድጋሚ ቢያቀርቡም ሰሚ አለማግኘታቸውን በቅጣቱ የተለየ ሃሳብ የያዙ ዳኛ ጭምር አረጋግጠዋል።