የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት ይቃወሙኛል የሚላቸውን የዲያስፖራ ቤተሰቦች ማሰሩን ቀጥሎአል

የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት ይቃወሙኛል የሚላቸውን የዲያስፖራ ቤተሰቦች ማሰሩን ቀጥሎአል
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 06 ቀን 2010 ዓ/ም) የሶማሊ ክልልን ህዝብ እንደ ግል ንብረቱ አይቶ ያሻውን እርምጃ ያለ ከልካይ እየወሰደ እንደሆነ የሚነገርለት የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ኢሌ ፣ አሁንም ይቃወሙኛል የሚላቸውን የዲያስፖራ አባላት ቤተሰቦችን ማሰሩን መቀጠሉን ምንጮች ገልጸዋል።
እንግሊዝ አገር የሚኖረውና የአብዲ ኢሌን አገዛዝ በመቃወም ትችት የሚያቀርበው አብዲራሽድ አሊ ሹዋ ዘመዶች ትናንት በጄ/ል አብዱለርሃማን ላባ ጎሌ ተይዘው ታስረዋል። 15 የሚሆኑ የአቶ አብድራሽድ ቤተሰቦች ቀደም ብሎ ታስረው ግፍ እየተፈጸመባቸው ነው።
4ቱ ሰዎች የ100 ዓመት እድሜ ያላቸውና በጸና ታመው አልጋ ላይ የሚገኙትን አጎታቸውን ሃጂ አልጉህዳድ ካባዲሌን ለመሰናበት ተሰብስበው በነበሩበት ወቅት መያዛቸውን የገለጹት ምንጮች፣ ሰዎቹ ከመታሰራቸው በፊት አብዲ ኢሊ የአጎቱ ልጅ የሆነውን የልዩ ፖሊስ አዛዥ ጄ/ል አብዱልራህማንን በመላክ አብዱልራሺድ በእሱ ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ እንዲያቆምና ይቅርታ እንዲጠይቅ ዘመዶቹ የማግባባት ስራ እንዲሰሩ፣ ይቅርታ ከጠየቀ የታሰሩት ሌሎች ሰዎች ከእስር እንደሚፈቱ ለማድረግ ሙከራ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጅ የአቶ አብዱላራሺድ ቤተሰቦች ይህንን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸው ፕሬዚዳንቱን ለማናገር ከቀብሪዳሃር ወደ ጅጅጋ የተጓዙ ቢሆንም፣ አቶ አብዲ ሰዎቹ “ ጄል ኦጋዴን” ወይም የኦጋዴን እስር ቤት ተብሎ በሚጠራው አስከፊ እስር ቤት እንዲገቡ አድርጓል።
ኢሳት ከ20 በላይ የታሰሩ የዲያስፖራ ቤተሰቦች ስም ዝርዝር የደረሰው ሲሆን፣ የእስረኞቹ ቁጥር በመቶዎች እንደሚቆጠር ምንጮች ይናገራሉ።
አብዲ ኢሌ በለመደው ይቅርታ የማስጠየቅ ስልት ተጠቅሞ ትናንት የጥፋተኝነት ቅጽ አስሞልቶ ኮ/ል ሃሰን አሊ ሃሰንንና አቶ ጊዲ ጎህን መልቀቁ ታውቋል። ኮ/ል ሃሰን የቀድሞው የመደበኛ ፖሊስ ኮማንደር የነበረ ሲሆን፣ አብዲ አሊ ፕሬዚዳንት እንደሆነ በመጀመሪያ ከስልጣን ያባረረው ሰው ነው። ኮ/ል ሃሰን ከስልጣን እንደተነሳ በጎሳው አባላት ሱልጣን ተብሎ የተሾመ ሲሆን፣ አብዲ ኢሌ የሱልጣኑን መሬት በመውረስ ለዘመዶቹ ማከፋፈሉን ምንጮች ይናገራሉ። ሌላው በይቅርታ የተፈታው ጌዲ ጎህ ደግሞ በክልሉ ብቸኛው የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ሲሆን፣ በውጭ የሚገኙ ሶማሊ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ማሰማት ሲጀምሩ ተይዞ ታስሯል።
ከውጭ አገር የአቶ አብዲ ኢሌ ተወካዮች በመሆን ቤተሰቦችን እንዲታሰሩ ከሚያደርጉት መካከል በአሜሪካ የፖስታ አግልግሎት ሰራተኛ የሆነው ባዲ ዩሱፍ ኢሴ፣ አብዱል ቡዱል አሳድ በደል እና የአሜሪካ ማህበራዊ ዋስትና ሰራኛ የሆነው ሞሃመድ ሃጉፍ መሆናቸው ታውቛል።
ያለ ምንም ተጠያቂነት በሶማሊ ክልል ህዝብ ላይ ጭፍጨፋ፣ እስራትና አሰገድዶ መድፈር እንዲፈጸም በማድረግ በአለም ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበበት ያለው አቶ አብዲ ኢሌ፣ ለህወሃት ጄኔራሎች እንደ ግል ሃብቱ የሚያየውን የክልሉን ባጀት እያወጣ በየጊዜው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየሰጠ ስልጣኑን ማቆየቱን የአካባቢው ተወላጆች ይናገራሉ። ይህንን ህገ ወጥ ተግባር ለማስቆም በሶማሊኛ “ ዱልሚዲድ” እየተባለ የሚጠራ አለማቀፍ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፣ የዚህ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ በክልሉ የሚኖሩ ሰዎች እና የዲያስፖራ አባላት ታሰረዋል።
በእስር ላይ ከሚገኙ ታዋቂ ሰዎች መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሃሰን አብዱላሂ ባዴና ጄኔራል ሙሃመድ አሊ ሃሰን ተጠቃሾች ናቸው። ጄ/ል ሙሃመድ የፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩና በአቶ አብዲ ትዕዛዝ የተባረሩ ሲሆን፣ ደ/ር ሃሰን አብዱላሂ ደግሞ የዱልማዲስ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት የሙሃመድ ባዴ የአጎት ልጅ በመሆናቸው ነው።