የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የፍትህና የአስተዳደር አካላት፤ የህዝብን አመኔታ አጥተዋል አለ

የካቲት 15 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፀረ-ሙስና ኮሚሽን መንግስት ላይ ያነጣጠረ ጠንካራ ጥናት ይፋ ሲያደርግ፤የአሁኑ  የመጀመሪያ ነው ተብሏል። “ኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን ሊሚትድ”ተሰኘ የታንዛኒያ ኮርፖሬሽን ነው ፤ለኮሚሽኑ ጥናቱን የሠራለት።

“ሁለተኛው አገር አቀፍ የሙስና ቅኝት”በሚል መሪ ሀሳብ ኩባንያው በ 27 የኢትዮጵያ ተቋማት ዙሪያ በሰራው በዚህ ጥናት፤’6 ሺህ 500 ሰዎችና ተቋማት ቃለ-ምልልስ በመስጠትና ሀሳባቸውን በመግለጽ ተሳታፊ ሆነዋል።

እንደ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሪፖርት፤ በ27 ተቋማት ላይ  በተካሄደው በዚህ ጥናት” ህብረተሰቡን የሚያስደስት አገልግሎት መስጠት ያልቻሉና በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያጡ ”ተብለው  ከ 22ኛ እስከ 27ኛ በማግኘት በመጨረሻ የተቀመጡት አምስት ተቋማት፤ ፖሊስ፤ፍርድ ቤቶች፣የጉምሩክ ባለስልጣን፣ የወረዳ መስተዳድሮችና ማዘጋጃ ቤቶች ናቸው።

የአንድ መንግስት የፍትህና የአስተዳደር አካላት የህዝብን አመኔታ አጥተዋል ማለት ፤ያ መንግስት ወድቋል ወይም በውድቀት አፋፍ ላይ ይገኛል እንደማለት ነው ይላሉ-አንድ የኮሚሽኑን ጥናት የተመለከቱ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ለኢሳት በሰጡት አስተያዬት።

በኢትዮጵያ የፍትህና አስተዳደራዊ መዋቅሩ በኢህአዴግ ተጽዕኖ ስር በመውደቁ ዜጎች ነፃ ዳኝነትና ማህበራዊ አገልግሎት ሊያገኙ እንዳልቻሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላለፉት ዓመታት ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በምርጫ 97 ወቅት ቅንጅት ለኢህአዴግ ካቀረባቸው ስምንት ጥያቄዎች መካከል አንዱ፤የዳኝነትና የፍትህ ስርዓቱ እንደገና በነፃነት የሚዋቀርበት መንገድ ይመቻች የሚል ቢሆንም፤ኢህአዴግ ጥያቄውን “ህገ-መንግስታዊን ሥርዓት ከመናድ ጋር በማገናኘት” ተቃዋሚዎችን ለማሰር እንደ አንድ የክስ ጭብጥ እንዳደረገው ይታወሳል።

እነሆ ፤ይህ በሆነ በስድስት ዓመቱ ነው ራሱ ያቋቋመው የፀረ-ሙስና ኮሚሽን  ፦የኢትዮጵያ የፍትህና የአስተዳደር አካላት የህዝብን ዓመኔታ አጥተዋል የሚል ሪፖርት ይፋ ያደረገው።

በኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ጥናት መሰረት፤ከ27ቱ ተቋማት መካከል ኅብረተሰቡን በሚያረካ ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ በመባል  ጥሩ ደረጃ ላይ የተቀመጡት፤  የፖስታ አገልግሎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ናቸው።

እነዚህ ተቋማት  ከመሰረት አጣጣላቸው ጀምሮ ተገንብተው ያደጉት በዓፄ ሀይለሥላሴ ሥርዓት እንደሆነ ያመለከቱት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ፤ ይህ ለአሁኖቹ መሪዎች እንደ ውርደት የሚቆይ ታሪክ ነው ብለዋል።

የኩባንያው የመጨረሻው ረቂቅ ጥናት   ይፋ የሆነው፤ ከሁለት ቀን በፊት ነው።

በሌላ ርዕስ በኢትዮጵያ ስር የሰደዱ ችግሮች ተብለው በጥናቱ  ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ የተዘረዘሩት፤ የዋጋ ግሽበት (የኑሮ ውድነት)፣ ሥራ አጥነት፣ የትራንስፖርት እጥረት፣ የመንገድ አውታር ያለመስፋፋትና የምግብ እጥረት ሲሆኑ፤ሙስና በሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

እንደ ሪፖርተር ዘገባ፤ጥናቱን ለማሰራት 468,000 ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ ወጪውን የሸፈነው የዓለም ባንክ ነው።

“ ኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን “ ይህን ጥናት እንዲሠራ የተመረጠውም፣ የዓለም ባንክ ያወጣውን ጨረታ ከተወዳዳሩ 20 ኩባንያዎች መካከል ባቀረበው ዋጋ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ተገልጿል።

ይህ ጥናት ከቀረበ በኋላ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ተወካዮች በጥናቱ ላይ ውይይት ሲያደርጉ፤ ፖሊስን ወክለው በስፍራው የተገኙት ምክትል ኮማንደር ባሳዝነው መንግስቴ፦”ፖሊስ ህገ-መንግስቱን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ነው” በማለት ፤በ ጥናቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ገልጸዋል።

ሆኖም፤  መንግስት ጥናቱን አስመልክቶ እስካሁን የሰጠው  ኦፊሴላዊ መግለጫም ሆነ አስተያዬት የለም።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide