የምርጫ ምዝገባ መጠናቀቁ በይፋ ከተገለጠ በሁዋላ ምዝገባው ዛሬም ቀጥሎአል

ጥር ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት የምርጫ ምዝገባው 100 በመቶ የተሳካ በመሆኑ ምርጫውን ከሁለት ቀናት የበለጠ እንደማያርዝም ገልጾ ነበር። ኢሳት ለምርጫው ተገዶም ቢሆን የተመዘገበው ህዝብ ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ የምርጫ ቦርድ የውስጥ ምንጮችን በመግልጽ ዘግቧል።

ከፍተኛ የኢህአዴግ ካድሬዎች ለወረዳ አመራሮች ቀይ መብራት በርቶባችሁዋል በማለት ማስፈራራታቸውን ተከትሎ ፣ አመራሩ ወደ ህዝቡ በመውረድ በእየቤቱ ሲያስገድዱ ቆይተዋል። ባለፈው ሳምንት ለኢህአዴግ የወረዳ አመራሮች በተላለፈው መመሪያ ደግሞ ለስራ ጉዳይ ወደ ቀበሌዎች የሚሄዱ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን የቀበሌ ሹሞች እንዲያጠሩ መመሪያ ተላልፎላቸዋል።

ኢሳት የምርጫው ምዝገባ ከተጠናቀቀ ከሳምንት በሁዋላ ፣ ዛሬ ጥር 30፣ 2005 ዓም በደቡብ ክልል የወረዳ አመራሮች እየዞሩ የምርጫ ካርድ ሲያድሉ ውለዋል። ነዋሪዎች እንደሚሉት ዛሬ የተካሄደው ምዝገባ የንግድ ድርጅቶችን ማእከል ያደረገ ነው።