የሙስሊም እንቅስቃሴ መሪዎች ታስረው ተለቀቁ

ሐምሌ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ መንግሥት የደህንነት ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ችግሮች አስወጋጅ ጊዜያዊ ኮሚቴ አባላት የሆኑትን አህመዲን ጀበል እና ዑስታዝ አቡበከር አህመድን ለግማሽ ቀናት አስሮ ለቀቀ፡፡

የእሥሩ ምክንያት በመጪው እሁድ በአወሊያ መስኪድ ያዘጋጁትን የአንድነትና የመጅሊስ ይፍረስ ተቃውሞ ስብሰባን እንዲያቋርጡ ለማድረግ ነው ሲሉ ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡

ሁለቱ የኮሚቴ አባላት ለእሁድ ሕዝባዊ የጸሎትና የመጅሊስ ይፍረስ የተቃውሞ ዝግጅት የኮሚቴ ስብሰባ ለማድረግ ከጠዋቱ 3፡30 ሰዓት ላይ በመኪና በሚጓዙበት ጊዜ ነበር ዘነበወርቅ አካባቢ የደህንነት ኃይሎች በፒክ አፕ መኪና በመከተልና መንገድ በመዝጋት እንዲወርዱ ያስገደዷቸው።  መሪዎቹም ማንነታችሁን ሳናውቅ ከመኪና አንወርድም በማለት በር ዘግተው የተቀመጡ ሲሆን የደህንነት ኃይሎች የመኪናውን በር በኃይል በመደብደብና መታወቂያቸውን በማሳየት አስወርደዋቸዋል፡፡

በቀጥታም በደህንነት መኪና ሁለቱንም ተወካዮች ጭነው ማዕከላዊ አጠገብ ወደ ሚገኘው አዲሱ የፖሊስ ህንፃ በማስገባት ሁለቱንም በተለያየ ቦታ ለብቻቸው እስከ ቀኑ 7፡30 ሰዓት ድረስ አስረዋቸዋል ፡፡

በቁጥጥር ሥር ካዋሏቸው በኋላም “የት ተማርክ፣ የት ነው የምትኖረው፣ የጅማውን ብጥብጥ የት ሆነህ ነው የመራኸው?” የሚል የተናጥል ጥያቄ ካቀረቡላቸው በኋላ፣ ” ከዚህ በኋላ መንግሥት ትዕግስቱ አልቋል ይገላችኋል፣ ለእሁድ ያሰባችሁትን ደርሰንበታል- ብታቆሙት ይሻላል አለበለዚያ ኃላፊነቱን ትሸከማላችሁ፣ ከዚህ በኋላ መንግሥት ለእናንተ ማስጠንቀቂያ አይሰጥም፤ የተፈራችሁ እንዳይመስላችሁ አንድ ባንድ ትለቀማላችሁ- ትገደላላችሁ፣ ከዚህ በኋላ ምርጫ የሚባል ነገር አቁሙ፣ ህዝቡ በአንድነት ኢህአዴግን መርጧል፣ እናንተን የመረጠ ህዝብ የለም የመጅሊስ ምርጫ በቀበሌና በወረዳ ይካሄዳል፣ ከዚህ በኋላ ሰደቃ፣ አንድነት፣ ስብሰባ የምትሉትን ሁሉ አቁሙ በማለት አስፈራርተው ለቀዋቸዋል።

መሪዎቹም ለጠቅላላው የኮሚቴ አባላትና ለህዝበ ሙስሊሙ በማሳወቅ እስከ ሞት ድረስ መስዋዕትነት በመክፈል ሃይማኖታችንን ከኢህአዴግ ጣልቃ ገብነት እንከላከላለን በማለት ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡

በዛሬው እለት ደግሞ 4ቱ በደህንነቶች ታፍነው ከተወሰዱ ከሰዓታት በሁዋላ  በማስፈራሪያ ተለቀዋል።

ከታፋኞቹ አንዱ የሆኑት ኢስታል አህመዲን ጀቢል ከእስር ከተለቀቁ በሁዋላ ባሰራጩት ጽሁፍ፦” ደህንነቶቹ ከወሰዱኝ በሁዋላ…እኛ እዚህ ያመጣንህ ለስብሰባ አሊያም እንድትናገር አይደለም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ልንሰጥህ ነው:: በየመስጂዱ የምታደርገውን የማስተባበር ስራ አቁም! አለበለዚያ ዋጋህን ታገኛለህ! አሉኝ” ብለዋል።

“ ….. በዚህ ጊዜ ጣልቃ ገባሁና  መረጃ ካላችሁ ፍርድቤት ዉሰዱና ጠይቁኝ እንጂ  ለምን ታስፈራሩኛላችሁ?  እኛ እንኳን ልንፈራ ለእምነታችን ህይወታችንን ለመስጠት ዝግጁ ነን አልኳቸው” ያሉት ኢስታል አህመዲን፤ “ ይህን ስላቸው ፤ላንተ ፍርድቤት በመውሰድ ጊዜ አናባክንም! ዋጋህን እንሰጥሃለን! አንዲት ችግር ቢፈጠር ፤የመጀመሪያው ጥይት አንተ ላይ ነው የሚያርፈው!! ትሰማ እንደሆን ስማ!! በማለት ሊያስፈራሩኝ ሞከሩ” ብለዋል።

ከዚያም፦  “…ካዋጣችሁ ቀጥሉ “ የሚል  ምላሽ መስጠታቸውን የጠቆሙት የኮሚቴ አባሉ፤ በመጨረሻም ፦ “ታርፍ እንደሆነ እረፍ! አላርፍም ካልክ በህይወት እንደፈረድክ እወቅ !’ ብለው እንዳሰናበቷቸው አመልክተዋል።

ይህን በሚሏቸው ጊዜ እርሳቸውም  በድጋሜ  ፦” ካዋጣችሁ ቀጥሉ!”  ማለታቸውን የጠቀሱት አቶ  ኢስታል፤ ከዚህ ሁሉ ማስፈራሪያ በሁዋላ  ለቀዋቸው መምጣታቸውን  ገልጸዋል።

አቶ ኢስታል  በጽሁፋቸው መጨረሻ ፦ “የዋህ ሰዎች!!! ህጋዊውንና ህገመንግስታዊውን የህዝበ ሙስሊሙን መብትን የማስከበር ሂደት በተራ ማስፈራሪያ ሊያቆሙት ይሞክራሉ እንዴ!? በመገረም እራሴን ጠየኩ” ብለዋል።

ከስድስት ወራት በላይ ያስቆጠረው የሙስሊሞች “የመብታችን ይከበር!” እንቅስቃሴ ካለፉት ጥቂት  ሳምንታት ወዲህ   በመላ አገሪቱ ዳግም እያገረሸ እንደሚገኝ ይታወቃል።

በመሪዎች ላይ የሚደረገውን ወከባ እና ማስፈራሪያ ሙስሊሙ በነገው እለት በነቂስ ወጥቶ እንዲቃወም የተለያዩ ወረቀቶች እየተበተኑ፣ መልእክቶች በፌስ ቡክ እየተሰራጩ ነው።

በሌላ በኩልም የህዝበ ሙስሊሙ ኮሚቴ መሪዎች ከታሰሩ ምን መደረግ እንዳለበት የሚገልጥ ወረቀት በስፋት እየተሰራጨ ነው።

በዚሁ ወረቀት ላይ መሪዎቹ ቢታሰሩ ፣ ሰላማዊ ትግሉ ያለምንም መደናበር እንዲቀጥል፣ መሪዎች የሚደርስባቸውን ማስፈራሪያና ዛቻ በመረጃ ለህዝቡና ለሚዲያዎች ማሳወቅ፣ ለአለማቀፍ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች ማሳወቅ፣ ወደ ሚታሰሩበት ቦታ በመሄድ በመሰባሰብ ረብሻ ሳይፈጠር የጉዳዩን ግዝፈት ማንጸባረቅ፣ በመላው አገሪቱ ሰላማዊ ትግሉን ማጠናከር፣ በመንግስት ተቋማት ላይ ያሉ ሙስሊሞችና ፍትህ ወዳድ የሆኑ ክርስቲያኖች አድማ መምታት፣ በመጀመሪያ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች አድማ ማድረግ፣ በውጭ የሚገኙትም ተቃውሞ ማድረግ፣ ሚሉት ይገኙበታል።

ወረቀቱ በመጨረሻም ” ድል ያለመስዋትነት እንደማይገኝ ስለምናውቅ ለ34 ሚሊዮን ሙስሊም በቂ የሆነ እስር ቤት ወይም ልትገሉንም ከሆነ 34 ሚሊዮን ጥይት አዘጋጁ ወይም ጥያቄያችንን ሳይሸራረፉ መልሱልን” ይላል።

በደሴ ከተማ የተያዙት ሼህ መከተ ሙሴ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም። በርካታ ሙስሊም ወጣቶችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide