የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚሰሩዋቸው ቤቶች በአመት በሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ እንደሚከራዩ ሰነዶች አመለከቱ

መጋቢት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚሰሩዋቸው ቤቶች በአመት በሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ እንደሚከራዩ ሰነዶች አመለከቱ

 የኢሳት የምርመራ ክፍል  በአዲስ አበባ ከተማ የሚሰሩ ህንጻዎችን ባለቤቶች ለማወቅ ባደረገው ጥረት የተወሰኑትን ህንጻዎች ባለቤቶችና የወጣባቸውን ወይም የሚወጣባቸውን የገንዘብ መጠን ባለፈው የካቲት ወር ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

 በተለምዶ ቦሌ መድሀኒአለም እየተባለ በሚጠራው  ወይም ወረዳ አስራ ሰባት ውስጥ በምእረባዊያን የቤት ደረጃ የሚሰሩት ቤቶች 90 በመቶ የሚሆኑት በከፍተኛ ጄኔራሎች  ባለቤትነት የሚሰሩ ወይም ተሰርተው የተጠናቀቁ መሆናቸውን በስእል አስደግፎ አቅርቦ ነበር።

 ጄኔራል ወዲ አሸብር 55 ሚሊዮን ብር ፣ ጄኔራል ዮሀንስ ደግሞ 45 ሚሊዮን ብር፣ ኮሎኔል ታደሰ ደግሞ 30  ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ህንጻ በመገንባት ላይ መሆናቸውን በዝርዝር ቀርቦ ነበር።

 አንድ የመከላከያ አዛዥ ወርሀዊ ደሞዝ በአማካኝ 3 ሺ ብር ነው። እንደ ጄኔራል ወዲ አሸብር የመሳሰሉት ጄኔራሎች ምንም ሳይመገቡ፣ የቤት ኪራይ ሳይከፍሉ ወይም እድሜ ልካቸውን ምንም አይነት ወጪ ሳያወጡ የሚከፈላቸውን ወርሀዊ የመንግስት ደሞዝ እንዳለ በባንክ ቢያስቀምጡ ፣ ከሚያስገነቡዋቸው ዘመናዊ ህንጻዎች መካከል አንዱን ህንጻ ብቻ ለማስገንባት ቢያንስ ለ150 አመት  በህይወት መኖርና ሳያቋርጡ ማጠራቀም ግድ ይላቸዋል የሚል ዘገባ መቅረቡንም ተመልካቾች ያስታውሳሉ።

 ምንም እንኳ ኢሳት የእያንዳንዱ የህወሀት ጄኔራል ቤት ምን ያክል እንደሚከራይ ለማወቅ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም ሳይሳካለት ቆይቷል። ይሁን እንጅ የመከለከያ ሰራዊት ባለስልጣናት ለግንዛቤ ይሆን ዘንድ የአንድ ጄኔራል ቤት የኪራይ መጠንን የሚያሳይ ማስረጃ ልከው እጃችን ላይ ደርሷል።

 ቤቱ በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ ወረዳ 17 ቀበሌ 20 በቤት ቁጥር 1185 የፖስታ ሳጥን ቁጥር 416 ይገኛል። የቤቱ ባለቤት ብርጋዴር ጄኔራል ፍሰሀ ኪዳኑ ይባላሉ። ጄኔራል ፍሰሀ በሌላ መኖሪያ ቤት ውስጥ በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 04፣ የቤት ቁጥር 931 ይኖራሉ።

 ጄነራሉ ቤታቸውን ለአፍሪካዊቱ አገር ስዋዚላንድ ኢምባሲ አከራይተዋል። በውሉ አንቀጽ 5 ላይ እንደተመለከተው የቤት ኪራዩ በወር የመነሻ ሂሳብ 5 ሺ 500 የአሜሪካን ዶላር ወይም በኢትዮጵያ ብር 95 ሺ 500 ብር ነው።  የስዋዚላንድ ኢምባሲ ለአከራዩ የአመት የቤት ክራይ ክፍያ 66 ሺ ዶላር ወይም 1 ሚሊዮን 147 ሺ 119 ብር በአንድ ጊዜ የቅድሚያ ክፍያ መክፈል እንደሚገባቸው በውሉ ላይ ተካትቶአል።  ተከራዩ ድርጅት ክፍያውን የሚከፍለው የሶስት ወሩን አንድ ጊዜ ሲሆን ይህም አሀዝ ወደ 300 ሺ ብር ይጠጋል።

 ጉዳዩን በማስመለከት ለብርጋዴር ጄኔራል ፍሰሀ ኪዳኑ ጥያቄ አቅርበንላቸው ለስዋዚላንድ ኢምባሲ የአከራዩት ቤት የእርሳቸው እንደሆነ፣ አሁንም በመከላከያ ስራ ላይ በማገልገል ላይ መሆናቸውን፣ ቦታው ለእርሳቸውና ለመሰሎቻቸው ከመንግስት የተሰጣቸው ለአገር ባደረጉት አስተዋጽኦ መሆኑን ከዚህ ውጭ ሰፊ ዝርዝር ማብራሪያ  ለመስጠት በአካል መገኘት እንዳለብን ገልጠዋል ።

 ከ90 በመቶ ያላነሰው ኢትዮጵያዊ በቀን  ከአንድ ዶላር በታች በሆነ ገቢ ይተዳደራል። ከሶስት አመት በፊት ጀምሮ በሚታየው የዋጋ ንረት ደግሞ ቀላል የማይባል ህዝብ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ለመመገብ ተገዶአል።

 በርካታ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ምሳ መብላት አልችል ብለው በክፍል ውስጥ እንደሚወድቁ፣ በርካታ ታዳጊ ወጣቶችም አንድ ድንች ብቻ በልተው የከሰአት ትምህርት እንደሚማሩ ፣ መምህራንም ለችግረኛ ተማሪዎች በማህበር ተደራጅተው ገንዘብ በማዋጣት የምሳ መግዢ ገንዘብ እንደሚለግሱ መረጃዎችን ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል።

 ኢትዮጵያ ለአብዛኛው ህዝብ ሲኦል፣ ለጥቂቶች ደግሞ ገነት እየሆነች መምጣቷን በርካታ ታዛቢዎች ሲገልጡ ቆይተዋል።

በቀርቡ ፋይናንሻል ኢንተግርቲ ባካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ በእየአመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ50 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ እየተመዘበረ በህገወጥ መንገድ ከአገር ይወጣል። በአለፉት 7 አመታት ከ170 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተዘርፎ ወደ ውጭ ተልኮአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide