የመንግስት ሰራተኞች ምርጫ ካርድ መውሰድ አለመውሰዳቸውን እየተጠየቁ ነው

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች በሚያዝያ ወር ለሚካሄደው የአካባቢና የአ/አ አስተዳደር ምርጫ ካርድ መውሰድና አለመውሰዳቸውን በቀጥታ እየተጠየቁ መሆኑን እንዲሁም አንዳንድ አባል ያልሆኑ ነዋሪዎች በካድሬዎችና በደህንነት ሰዎች የኢህአዴግ ዕጩ ሆነው በምርጫው እንዲቀርቡ ግፊት እየተደረገባቸው
መሆኑን ምንጮች አመለከቱ፡፡

ለአንድ ወር ተካሄዶ ጥር 21 ቀን 2005 ዓ.ም የመራጮች መደበኛ ምዝገባ ቢጠናቀቅም በተለይ በአዲስ አበባ አስተዳደር የተመዘገበው ሕዝብ ቁጥር እጅግ ከተጠበቀው በታች መሆን ገዥውን ፓርቲ አስደናግጧል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የግንባሩ አባላትና ደጋፊዎች በአዲስአበባ አስተዳደር በሚገኙ ቢሮዎች የሚሰሩ ሰራተኞችን ቢሮ ለቢሮ በመሄድ የምርጫ ካርድ መውሰድ አለመውሰዳቸውን በመጠየቅና በማጣራት ላይ ናቸው፡፡

እንደ ምንጮቻችን ገለጻ ከሆነ ካርድ አልወሰድንም የሚሉትን ሰራተኞች ካድሬዎቹ ለምን እንዳልወሰዱ ምክንያታቸውን በመጠየቅ እንዲወስዱ እያግባቡዋቸው ይገኛሉ፡፡ ይህ ድርጊታቸውም በይፋ የመራጮች መደበኛ የምዝገባ ቀነ ገደብ ከተጠናቀቀና ቦርዱ ካቀድኩት በላይ መራጭ ተመዝግቦልኛል ብሎ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከገለጸ በኋላ መከናወኑ አስገራሚ አድርጎታል፡፡

አንድ የአስተዳደሩ ባልደረባ ስለሁኔታው ሲያስረዳ “አንድ ካድሬ በግልጽ መጥቶ ምርጫ ካርድ መውሰዴንና አለመውሰዴን ጠየቀኝ፡፡ለምን ትጠይቀኛለህ ስለው ምርጫ ላይ መሳተፍ ለስራ ዕድገትም ይጠቅምሃል፡፡አንተ ደግሞ ጥሩ አፈጻጸም ያለህ ሰራተኛ በመሆንህ ካርድ አለመውሰድህ ሌላ ነገር እንዳያመስልብህ ልመክርህ ብዬ ነው” የሚል መልስ
እንደሰጠው አስረድቷል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም ከአራት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉኝ የሚለው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አባል ያልሆኑ ሰዎችን ለምርጫው ኢህአዴግን ወክላችሁ እንድትቀርቡ ታጭታችሃል በሚል በተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ ግለሰቦችን በግል ስልካቸው ጭምር በመወትወት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

በአካባቢና በአዲስአበባ ምርጫ የዕጩዎች ብዛት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር መሆኑና ያሉት አባላትም ጥራት የላቸውም የሚል ትችት የሚቀርብባቸው መሆኑ ግንባሩን ፊቱን ወደ አዲስ
አባላት ምልመላ እንዲያዞር ሳያደርገው እንዳልቀረ ይገመታል፡፡

ምርጫ ቦርድ ካቀድኩት በላይ መራጮች ተመዝግበውልኛል ሲል በቅርቡ መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

የኢሳት የደቡብ ዘጋቢ እንደገለጠው ዛሬም ድረስ በክልሉ የምርጫ ካርድ የወሰዱና ያልወሰዱ ሰዎች እየተለዩ ካርድ ሲሰጣቸው ውሎአል።