የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ስጋት ገብቶናል አሉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 3/2011)የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች የከተማዋ ጸጥታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ስጋት ገብቶናል ሲሉ ገለጹ።

ኤጄቶ በሚል የሚንቀሳቀሱ የሲዳማወጣቶች ስም የተደራጁ ሃይሎች የአካባቢውን ነዋሪ እያዋከቡ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ምሬታቸውን ገልጸዋል።

ኢሳት ያነጋገረውና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የኤጄቶ አባል አንዳንድ የሲዳማን ወጣቶች መልካም ስም ለማጉደፍ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት እንዳሉ ተናግሯል።

ሰሞኑን በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ያጡ 5 የሲዳማ ወጣቶችን ሃዘን ከመግለጽ ጋር ተያይዞ የከተማዋ ትምህርት ቤቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስራ እንዲያቆሙ በኤጄቶ ስም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በማስገደዳቸው ከተማዋ ውጥረት ውስጥ መግባቷን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የከተማዋ አስተዳደር በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጠን ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃዋሳ ነዋሪዎች ተሳቀን እንድንኖር ተገደናል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ለሃዋሳ ነዋሪ ስጋትና ፍርሃትን ይዞብን መጥቷል፣ ከተማዋ የእኛ ናት በሚሉ አንዳንድ ወገኖች የተነሳ ወጥቶ በሰላም መግባት አስቸጋሪ እየሆነ ሲሉ ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ ናቸው።

የኤጄቶ የማህበራዊ ድረገጽ ላይ በኢጄቶ ስም እየተፈጸመ ያለውን ረብሻና አድማ የሚያወግዝ መልዕክት ተላልፏል።

ከኤጄቶ እውቅና ውጪ ረብሻዎች፣አድማዎችና ትንኮሳዎች እንዲፈጸም የሚያደርጉ ሃይሎች የኤጄቶን ጥያቄ አቅጣጫ ለማሳት ነው ሲል በገጹ ላይ አስፍሯል።

በዚህ ዙሪያ የከተማው አስተዳደር ምላሽ የሚሰጠን ከሆነ ኢሳት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑንም እንገልጻለን።