የሎስ አንጀለሱ ታዋቂ ራፐር ኤርምያስ አስገዶም በተተኮሰበት ተገደለ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 30/2011) በአባቱ ኤርትራዊ ደም ያለውና የሎስ አንጀለሱ ታዋቂ ራፐር ኤርምያስ አስገዶም (ኒፕሲ ሐስል) በተከፈተበት ተኩስ መገደሉ ተነገረ።

የ33 ዓመቱ ራፐር በርካታ ቦታዎች ላይ በጥይት መመታቱን እና ሆስፒታል እንደደረሰ ሕይወቱ ማለፉን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

ኤርምያስ አስገዶም (ኒፕሲ ሐስል)  ሎስአንጄልስ ወስጥ በባለቤትነት በሚያስተዳድረው ማራቶን የአልባሳት መደብር  በስድስት ጥይት ተበሳስቶ ሲገደል ሌሎች ሁለት ሰዎችም በተተኮሰባቸው ጥይት ቆስለዋል።

ከኤርትራዊ አባት እና ጥቁር አሜሪካዊ እናት የተወለደው ኤርሚያስ አስገዶም በዚህ ዓመት ለሽያጭ ያበቃው አልበሙ በግራሚ የምርጥ ራፕ አልበሞች ምርጫ ላይ እጩ ለመሆን በቅቶ ነበር።

የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚንስትሩ የማነ ገ/መስቀል የኤርሚያስ አስግዶም ሞት እጅጉን እንዳሳዘናቸው በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።ለቤተሰቦቹመ መጽናናትኝ ተመኝተዋል።

ኤርሚያስ ከአንድ ዓመት በፊት የትወልድ ሀገሩ የሆነችውን  ኤርትራ ጎብኝቶ እንደነበርም ተገልጿል።

ኤርሚያስ አስገዶም ተወልዶ ያደገው በደቡባዊ ሎስ አንጀለስ ሲሆን በተለያዩ የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችና በኪነጥበብ ስራዎቹ ይታወቃል።

ታዋቂው ራፐር ኤርምያስ አስገዶም (ኒፕሲ ሐስል) “ያደኩት በውንብድና ቡድኖች ውስጥ ነው” ሲል ለሎስ አንጀለስ ታይምስ በአንድ ወቅት ቃለ መጠይቅ ሰጥቶ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።

በዚሁ ቃለምልልስም “… ሞት፣ ግድያ የየእለት ትዕይንቶቻችን ነበሩ። በጦርነት ቀጠና ውስጥ እንደመኖር ነው፤ ከዚህ መንደር ሰዎች ሲሞቱ ከቁብ አይቆጠርም ነበር።” ብሎ እንደነበርም ዘገባው አስታወሷል።