የህዝብ ትምህርት ቤቶች ሊወረሱ ነው

ሚያዚያ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ መንግሥት በአዲስ አበባ እና በዋና ዋና የክልል ከተሞች የሚገኙ ነፃ የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን ወደ መንግሥት ትምህርት ቤትነት ለማዘዋወር ወይም ለመውረስ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤት መምህራኖችንና ሠራተኞችን  ረቡ እና ሀሙስ ማለትም ሚያዚያ 24 እና 25 ሙሉ ቀን ፣ የተማሪዎችን ወላጆችን ደግሞ ቅዳሜ እና እሁድ ለግማሽ ቀን ለይስሙላ አወያይቶ ትምህርት ቤቶቹ ወደ መንግሥት ባለቤትነት መሸጋገራቸውን ገልፆል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመንግሥት፣ የሕዝብ፣ የግል፣ የቤተ-ሃይማኖቶች እና የውጭ ኮሚዩኒቲ ማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች ናቸው በማለት ለዘጋቢያችን የገለጹ አንድ የወረዳ የትምህርት ቢሮ የትምህርት አመራር ባለሙያ ፣  መንግሥት በቁጥር በርከት ብለው የሚገኙ ነፃ የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን መውረስ የፈለገው ለትምህርት ጥራት ለማገዝ ሳይሆን ለፖለቲካ ጠቀሜታ ነው ብለዋል። ፖለቲካውን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ ኢኮኖሚውን፣ ፍርድ ቤትን፣ መገናኛ ብዙሃንን እና ቤተሰብን ሳይቀር በቅርብ እርቀት የሚቆጣጠረው ኢህአዴግ አሁን ደግሞ ትምህርት ቤት ላይ ከወትሮው ላቅ ባለ ሁኔታ ጠልቆ መግባት ፈልጓል ሲሉ አክለዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለፃ የኢህአዴግ መንግሥት በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚገኙ አብዛኛውን መምህርና መምህርት በጥቅማ-ጥቅም አስገዳጅነት የፓርቲ አባል አድርጎ ያጠመቀ ሲሆን ፣ አሁን ደግሞ በሕዝብ ትምህርት ቤት የሚገኙትን መምህራን ሁሉ በፓርቲ አባልነት ለማጥመቅ ትምህርት ቤቶቹን ቀድሞ በመውረስ መምህራኑን መጠቅለል ፈልጓል ይላሉ።

 ወደ መንግሥት ባለቤትነት አንሸጋገርም ያሉትን ጠንካራ የቦርድ አባላት ያሏቸውን የሕዝብ ትምህርት ቤቶች የኢህአዴግ መንግሥት ቀደም ሲል በትምህርት ቁሳቁስ፣ በመማሪያ መጽሐፍት እና የመምህራን ጉድለት ሲኖርባቸው በመቅጠርና ከመንግሥት ትምህርት ቤት በዝውውር የሚያሟላላቸውን ከዚህ በኋላ ወደ መንግሥት ባለቤትነት ካልተዘዋወሩ በቀር ትብብር እንደማያደርግ በደብዳቤ አሳውቋል ብለዋል ባለስልጣኑ፡፡

የኢህአዴግ መንግሥት ባወጣው አስገዳጅ ውል መሠረት የተደናገጡ የአዲስ አበባ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ለወላጆች በላኩት ደብዳቤ ላይ “… በአዋጅ 54/68 ወደ ሕዝብ ት/ቤት እንዲዞሩ ከተደረጉ ት/ቤቶች ውስጥ ተካተናል፣ በመሆኑም ለሚኒሥትሮች ምክር ቤት መጋቢት 14 ቀን 2004 ዓ.ም ቀርቦ ወደ መንግሥት ለማዛወር ህዝቡ ጋር ቀርቦ በፈቃደኝነት መሆን ስላለበት እና ልጅዎን በነፃ ለማስተማር ውሳኔ እንዲሰጡ ቅዳሜ ሚያዚያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም በትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ በመገኘት ምርጫዎን እንዲያሳውቁ …” የሚል ይዘት ያለው መልክት ተላልፎአል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide