የሃረማያ ዩኒቨርስቲ ፕረዚዳንት ፕ/ር ጨመዳ ፊኒንሳ ስልጣን ለቀቁ

የሃረማያ ዩኒቨርስቲ ፕረዚዳንት ፕ/ር ጨመዳ ፊኒንሳ ስልጣን ለቀቁ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 09 ቀን 2010 ዓ/ም) የሃረማያ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸው ተቀባይነት በማግኘቱ ከኃላፊነት ተስተዋል ። ፕ/ር ጨመዳ ሃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ለምን እንደፈለጉ በግልጽ ባይታወቅም፣ ከዩኒቨርስቲው ቦርድ ሰብሳቢ ከአቶ ስለሺ ጌታሁን ጋር ባላቻው አለመግባባት ይሆናል ሲሉ ምንጮች ይገልጻሉ። ሌሎች ወገኖች ደግሞ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በየጊዜው የሚነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ የጸጥታ ሁኔታውን ለመቆጣጠር በሚል የህወሃት የደህንነት ሰዎች የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በመሰልቸት እንደለቁ ይናገራሉ።
የሃረማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ በኢትዮጵያ በሚደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ሚና ከሚጫወቱ ተማሪዎች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። ፕ/ር ጨመዳ የአጋዚ ወታደሮችና የፌደራል ፖሊሶች ወደ ግቢው እየገቡ በተማሪዎች ላይ እርምጃ ይወስዱ በነበረበት ወቅት፣ ወታደሮቹ ወደ ግቢ እንዲገቡ ፈቃድ ሰጥተዋል በሚል ከፍተኛ ትችት ሲደርስባቸው ቆይቷል።
ዩኒቨርስቲውን ለ3 ዓመታት ያስተዳደሩት ፕ/ር ጨመዳ ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ፣ በምትካቸው ዩኒቨርሲቲውን የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጀማል ዩሱፍ በጊዚያዊነት ተሹመዋል።